ኀዳር ፳ (ሃያ) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ባለፈው ቅዳሜ፣ እሁድ እና ሰኞ ባል ድፍን አዲስ አበባ ጭለማ ውጧታል። ካለፉት ሁለት አመታት ወዲህ የሃይል መቆራረጡ እየተባባሰ የመጣ ሲሆን የመንግስት ሹማምንት አንዴ ችግሩ የመልካም አስተዳደር ብልሽት ውጤት ነው፣ ሌላ ጊዜ ደግሞ የመስመር እርጅና ነው እያሉ ፣ እርስበርሱ የተምታታ መግለጫ ከመስጠት ባለፈ ሁነኛ መፍትሄ ሳያበጁለት ቀርተዋል።
ችግሩ በተባባሰበት ባለፉት ሁለት ቀናት ዳቦ ቤቶች፣ የውበት ሳሎኖች፣ አነስተኛ ምግብ ቤቶች፣ካፌዎች፣ ክሊኒኮችና ጤና ጣቢያዎች፣ የባንክ ኤ ቲ ኤም ማሸኖች ከስራ ውጪ ለመሆን ተገደዋል።
የኢትዮጵያ መንግስት ህዝቡ በመብራት መቆራረጥ እየተሰቃየ ባለበት፣ ከችግሩጋር ተያይዞ ምርትና ምርታማነት ባሽቆለቆለበት በዚህ ወቅት መብራት ለጅቡቲ ፣ለኬንያ መሸጡ አይዘነጋም። መንግስት የመብራት ስርጭቱን በፈረቃ ለማድረግ ማቀዱን አስታውቋል። የመብራት መቋረጥ የተከሰተው በጣና በለስና በግልገል ጊቤ አንድ የኤሌክትሪክ ማመንጫ ላይ የቴክኒክ ችግር በመፈጠሩ ነው ብሎአል።