ኢሳት (ሃምሌ 29 ፥ 2008)
የአሜሪካ መንግስት አዲስ አበባ ከተማ በሚገኘው የሃገሪቱ ኤምባሲ የሚሰሩ ሰራተኞች ወደ ኦሮሚያ ክልል እንዳይጓዙ አሳሰበ።
በክልሉ ቅዳሜና እሁድ የተቃውሞ ሰላማዊ ሰልፍ እንደሚካሄድ በማህበራዊ ድረገጾች ቅስቀሳ እየተካሄደ መሆኑን የገለጸው የሃገሪቱ መንግስት ከኢምባሲው ሰራተኞች በተጨማሪ አሜሪካውያን በክልሉ ሊያደርጉ ባሰቡት ጉዞ ላይ አስፈላጊውን የጥንቃቄ እርምጃ እንዲወስዱ በጉዳዩ ዙሪያ ባወጣው መግለጫ አመልክቷል።
በኦሮሚያ ክልል ሊካሄድ የታቀደውን ይህንኑ የተቃውሞ ሰላማዊ ሰልፍ ተከትሎ የስልክና የኢንተርኔት አገልግሎት ሙሉ ለሙሉ ሊቋረጥ እንደሚችል የአሜሪካ መንግስት ገልጿል።
ከቀናት በፊት የካናዳ መንግስት ተመሳሳይ ማሳሰቢያን ለዜጎች ያሰራጨ ሲሆን፣ መቀመጫቸውን በአዲስ አበባ ያደረጉ የተለያዩ አለም አቀፍ ተቋማትና ኤምባሲዎች ለሰራተኞቻቸውና ለዜጎቻቸው የማሳሰቢያ መልዕክትን እያስተላለፉ እንደሆነ ለመረዳት ተችሏል።