በአዲስ አበባ የትራፊክ አደጋ ተከስቶ በሰውና በንብረት ላይ ጉዳት አደረሰ

ኢሳት (መጋቢት 26 ፥ 2008)

ሰኞ ጠዋት በአዲስ አበባ ከተማ ስድስት ተሽከርካሪዎችን ያካተተ የትራፊክ አደጋ በትንሹ የሶስት ሰዎች ህይወት እንዲያልፍ ማድረጉንና ከ20 የሚበልጡ ደግሞ ክፉኛ መጎዳታቸውን ፖሊስ አስታወቀ። በተለምዶ ኮልፌ 18 ማዞሪያ ተብሎ በሚጠራል አካባቢ በደረሰ በዚሁ አደጋ አራት የሚሆኑ የንግድ ቤቶችም ጉዳት የደረሰባቸው ሲሆን የሟቾች ቁጥርም ሊጨምር ይችላል ተብሎ ተሰግቷል።

ሲሚንቶ የጫነ ከባድ ተሽከርካሪ አድርሶታል በተባለው በዚሁ አደጋ ሶስት ተሽከርካሪዎች ሙሉ ለሙሉ ከጥቅም ውጭ የሆኑ ሲሆኑ የተቀሩትም ተሽከርካሪዎች ከባድ ጉዳይ እንደደረሰባቸው ታውቋል።

በዚሁ አደጋ እስካሁን ድረስ በትንሹ ሶስት ሰዎች በአሰቃቂ ሁኔታ የሞቱ መሆናቸውን የገለጸው ፖሊስ ሌሎች 22 ሰኦውችም ጉዳት እንደደረሰባቸው አመልክቷል።

በአደጋው ጉዳይ የደረሰባቸው ሰዎችም በጦር ሃይሎች በሌላ ሆስፒታል ህክምና እየተደረገላቸው የሚገኝ ሲሆን በመንገድ ዳር የነበሩ የመድሃኒትና ሌሎች የንግድ ተቋማትም መጎዳታቸውን ፖሊስ አክሎ ገልጿል።

በአካባቢው ተደጋጋሚ የትራፊክ አደጋ እንደሚደርስ የሚናገሩት ነዋሪዎች በበኩላቸው ጉዳዩ የሚመለከተው የመንግስት አካል መንገዱን በአግባቡ እንዲገነባ ጠይቀዋል።

የአዲስ አበባ መንገዶች ባለስልጣን በበኩሉ በስፍራው የሚገኘውንና ለበርካታ የትራፊክ አደጋ ምክንያት የሆነውን አደባባይ በተያዘው አመት በአዲስ መልክ ለመገንባት እቅድ መኖሩን አስታውቋል።