ኢሳት (የካቲት 21 ፥ 2008)
በአዲስ አበባ ከተማ አገልግሎትን በመስጠት ላይ ይሉ በሺዎች የሚቆጠሩ የታክሲ አሽከርካሪዎች ተግባራዊ የተደረገን አዲስ የትራፊክ ቁጥጥር ደንብ በመቃወም ሰኞ የስራ ማቆም አድማ ጀመሩ።
የታክሲ አሽከርካሪዎች የወሰዱትን እርምጃ ተከትሎም የከተማዋ ነዋሪዎች የዕለት ከእለት የኑሮ እንቅስቃሴያቸው መስተጓጎሉን እማኞች ገልጸዋል።
ከአራት አመት በፊት የወጣውና ከቀናት በፊት ተግባራዊ መደረግ የጀመረው የትራፊክ መቆጣጠሪያ ደንብ ለስራ አስቸጋሪ በመሆኑ ደንቡ መሻሻል እንዳለበት የታክሲ አሽከርካሪዎች አስታውቀዋል።
በአዲሱ መመሪያና ደንብ ዙሪያ በቂ ውይይት አለመካሄዱን የሚናገሩት አሽከርካሪዎች ጉዳዩ የሚመለከተው አካል ደንቡን በአስቸኳይ እንዲያጤነውም ማሳሰባቸውን ከሃገር ቤት የተገኘ መረጃ አመልክቷል።
በደንቡ ላይ ማሻሻያ ካልተደረገ የጀመሩት አድማ እንደሚቀትሉ የገለፁት የታክሲ አሽከርካሪዎች የፌዴራል ትራንስፖርት ባለስልጣን ምላሽን እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል።
ሰኞ ረፋድ ላይ ይተጀመረውን የታክሲ አሽከርካሪዎች አድማ ተከትሎም ተማሪዎች የመንግስት ሰራተኞችና ሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎች በትራንስፖርት እጦት በየመንገዱ ሲጉላሉ መዋላቸው ታውቋል።
በጉዳዩ ዙሪያ ምላሽን የሰጠው የትራንስፖርት ባለስልጣን በበኩሉ በደንቡ ላይ ለአሽከርካሪዎች የግንዛቤ ማስጨበጫ ማብራሪያዎች ማድረግ ለላስፈለገ በማለት ደንቡ ለቀጣዮቹ ሶስት ወራቶች ስራ ላይ እንደማይውል አስታውቋል።
በከተማ የታክሲ አገልግሎት የሚሰጡ ወደ 10ሺ የሚጠጉ ታክሲዎች በስራ ማቆም አድማው ተሳታፊ መሆናቸውንም ለመረዳት ተችሏል።
የትራስፖርት ባለስልጣን ደንቡ ተግባራዊ እንደማይሆን ቢያሳውቅም ሰኞ ምሽት ድረስ በአዲስ አበባ ከተማ የትራንስፖርት እጥረቱ መቀጠሉን ከሃገር ቤት የተገኘ መረጃ አመልክቷል።
ይህ በእንዲህ እንዳለም፣ ሰኞ የተጀመረው የታክሲ አሽከርካሪዎች የስራ ማቆም አድማ በአዲስ አበባ ከተማ ዙሪያ ባሉ አነስተኛ ከተሞች መዛመቱን በሃገር ውስጥ ያሉ መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።