በአዲስ አበባ የተገነቡ ጥቂት ቤቶች ለቤት ፈላጊዎች ሊተላልፉ አልቻሉም ተባለ

ጥር ፳፫ (ሃያ ሦስት)ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በአዲስአበባ የቤቶች ልማት መርሃግብር አንዱ በሆነውና 40 በ60 እየተባለ የሚታወቀው ፕሮግራም ከ160 ሺ በላይ ሕዝብ ተመዝግቦ ቤቱን ለማግኘት እየተጠባበቀ ቢሆንም፣ የከተማው አስተዳደር የገነባቸውን ጥቂት ቁጥር ያላቸው ቤቶቹን ግልጽ ባልሆነ ምክንያት ለማስተላለፍ እንዳልቻለ ተመዝጋቢዎች ለዘጋቢያችን ገለጹ፡፡
አስተዳደሩ የ2007 ምርጫን ተከትሎ 1 ሺ 200 ገደማ ቤቶችን አስተላልፋለሁ በሚል ቃል የገባ ቢሆንም፣ ምርጫው ካለፈ በኋላ ጉዳዩ ተረስቶ እስካሁን ድረስ ቤቶቹ ለተጠቃሚዎች እንዳልተላለፉ ታውቋል፡፡ ነዋሪዎች “ ከዛሬ ነገ የቤት ባለቤት እንሆናለን በሚል ተስፋ ወርሃዊ ቁጠባችንን ሳናቋርጥ የቀጠልን ቢሆንም፣ አስተዳደሩ ግን ምክንያቱ እንኳን ምን እንደሆነ ሳይናገር ዝምታን መምረጡ አሳዝኖናል” ብለዋል፡፡ “በወርሃዊ ደመወዝ ቁጠባ እያደረግን፣ በግለሰብ ኪራይ ቤት ቤተሰቦቻችን እያስተዳደርን በከፍተኛ ችግር ውስጥ ነን” ያሉት አንድ አስተያየት ሰጪ፣ መስተዳድሩ የገባውን ቃል ባለማክበሩ አዝነናል ብለዋል፡፡
“ጥቂት የማይባሉ ዘመዶቻችንና ጓደኞቻችንን በመንግስት ድርጊት ተስፋ በመቁረጥ የጀመሩትን ቁጠባ እያቆሙ ይገኛል” ያሉት ሌላው አስተያየት ሰጪ፣ ስርዓቱ “ ቁጠባን አበረታታለሁ እያለ፣ በሌላ በኩል እየቆጠበ ያለውን ዜጋ ተስፋ እያስቆረጠው ነው” በማለት ሃዘናቸውን ገልጸዋል።
አስተዳደሩ በዘረጋው የቤት ልማት መርሃግብር መሰረት ለ40 በ60 መርሃ ግብር ወደ 160 ሺ ሕዝብ የተመዘገበ ሲሆን ፣ ከዚህ ቁጥር ውስጥ 11 ሺ 682 ያህሉ የተተመነውን ክፍያ መቶ በመቶ ፈጽመው ቤት የሚጠባበቁ ናቸው፡፡