ሚያዝያ ፲፭(አስራ አምስት) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-በሊቢያ በረሃና በደቡብ አፍሪካ በ አሰቃቂ ሁኔታ የተገደሉትን ኢትዮጵያዊያንን ለማሰብ ረቡዕ ሚያዚያ 15 ቀን 2007 ዓም መንግስት የጠራው ሰልፍ ወደ ሕዝባዊ ተቃውሞ በመለወጡ በብዙ መቶወች
የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን በፖሊሶች ተደብድበው ሆስፒታል ከገቡ በሁዋላ፣ በቦታው ላይ የተያዙ፣ ማሽት ላይ በየቤቱ እየተለቀሙ የተያዙ እንዲሁም ዛሬ ሃሙስ ጧት የተያዙ በየክፍለ ከተማው እስር ቤቶች በሺዎች የሚቆጠሩ የአዲስ አበባ ወጣቶች እና የዩኒቨርስቲ
ተማሪዎች በተለያዩ እስር ቤቶች ውስጥ እንደሚገኙ የደረሰን መረጃ ያሳያል።
በርካታ እስረኞች ከቀላል እስከ ከከባድ አካላዊ ጉዳት ደርሶባቸዋል። በከፍተኛ ሁኔታ የቆሰሉት ወደ ሆስፒታል ሲወሰዱ ፣ ሌሎቹ ግን ሌሊቱን በእስር ቤት ሜዳ ላይ በስቃይ እንዲያሳልፉ ተደርጓል። ወላጆች ምግብ እስከ ዛሬ ጧት ድረስ ምግብ እንዳያቀርቡ ተከልክለው
መዋላቸውን ገልጸዋል። በድፍን አዲስአበባ ከጧቱ 1 ሰአት እስከ ቀኑ 7፡ 30 መብራት የተቋረጠ ሲሆን የተንቀሳቃሽ ስልክና ኢንተርኔት
አገልግሎትም እንዲስተጓጎል በመደረጉ ግንኙነት ተቋርጦ ውሏል፡፡ በተመሳሳይ ሁኔታ ማምሻውን ከ2፡00 ሰዓት ጀምሮ መብራት ተቋርጦ ሌሊት ላኢ እንዲለቀቅ ሆኖአል፡፡ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሃይል ችግሩ የቴክኒክ ነው ቢልም
ያነጋገርናቸው የከተማዋ ነዋሪዎች ሆን ተብሎ ሕዝቡ እርስ በርሱ እንዳይገናኝ ለማድረግ ነው ይላሉ፡፡
ሰዎች አማራጭ የመገናኛ ብዙሃንን እንዳይከታተሉ እንዲሁም የሚፈለጉ ሰዎችን በምሽት ለማሰር እንዲመች ምሽት ላይ ሆን ተብሎ መጥፋቱን ነዋሪዎች ይገልጻሉ፡፡
በትላንቱ ዕለት ሕዝቡ በራሱ ተነሳሽነት ተቃውሞ ቢያሰማም፣ መንግስት ለህዝቡ ተቃውሞ ዕውቅና ላለመስጠት ሲል ከሀገር ውስጥ ሰማያዊ ፓርቲ ከውጪ ደግሞ ግንቦት ሰባት ከጀርባ መኖራቸውን በመጥቀስ ሕዝቡን ለማሳመን በመሞከር ላይ ይገኛል፡፡
ተቃውሞው አይኤስ ከገደላቸው ኢትዮጵያዊያን ሐዘን ጋር ብቻ ተያይዞ የሚታይ እንዳልሆነ፣ ህዝቡ ተቃውሞውን እንኩዋን መግለጽ የማይችልበት ደረጃ በመድረሱ ምክንያት የተከሰተ መሆኑን ዘጋቢያችን ያነጋገራቸው አስተያየት ሰጪዎች ገልጸዋል፡፡
አቶ ሃይለማርያ ደሳለኝ በመስቀል አደባባይ ተገኝተው ንግግር ለማድረግ በሚክሩም ህዝቡ ተቃውሞውን አሰምቷል። የህዝቡ ቁጣ እየገነፈለ በመምጣቱና ወጣቶች ባለስልጣኖች ወዳሉበት ቦታ መንቀሳቀስ ሲጀምሩ ባለስልጣናቱ በፍጥነት ከአካባቢው እንዲርቁ ተደርጓል።
የፌደራል ፖሊሶች ለሰልፍ በወጡ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ላይ በወሰዱት እርምጃ በመላው አገሪቱ ያሉ ኢትዮጵያውያን ቁጣቸውን ገልጸዋል።
በሌላ ዜና ደግሞ በተለያዩ የአውሮፓ አገራት የሚካሄዱ ተቃውሞወች ቀጥለዋል። በጣሊያን በደቡብ አፍሪካ እና በኢትዮጵያ ኢምባሲዎች ፊት ለፊት የተቃውሞ ሰልፍ ተካሂዷል። በበርሊንም ተመሳሳይ ሰልፍ መደረጉን ታውቋል።
የተለያዩ የፖለቲካና የሲቪክ ድርጅቶችም በሊቢያና በደቡብ አፍሪካ በኢትዮጵያውያን ላይ የተፈጸመውን አሰቃቂ ድርጊት በጥብቅ እያወገዙ ነው። አርዱፍ ሰሞኑን በኢትዮጵያውያን ላይ የተፈጸመውን እርምጃ በጽኑ አውግዞ፣ ኢትዮጵያውያን የፖለቲካ እና ሲቪክ ድርጅቶች
አንድነት በመፍጠር ለዚህ ሁሉ ተጠያቂ የሆነውን የኢህአዴግ አገዛዝ እንዲፋለሙ ጥሪ አቅርቧል። የአፋር የሰብአዊ መብቶች ድርጅትም በኢትዮጵያውያን ላይ የተፈጸመውን ወንጀል በጽኑ ኮንኖታል። ኢትዮጵያውያን በጋራ እንዲነሱም ጥሪ አቅርቧል።
አርበኞች-ግንቦት 7 በበኩሉ ”ያዋረደን፣ በአይ ሲስ ቢላዋ ያሳረደን ህወሓት ነው። እንደ አገርና እንደ ሕዝብ የደረሰብን ውርደት የትም ብንሄድ የምናመልጠው አልሆነም”ካለ በሁዋላ፣ “በሀይማኖት፣ በብሔር፣ በጾታ ልዩነት ሳታደርግ ዛሬ በአንድነት እንደተሳህ አንድነትህን እንደጠበቅህ ቀጥል፣ የጀመርከው ትግል እዳር ሳይደርስ እረፍት የለንም።”ብሎአል።
ሰማያዊ ፓርቲ ደግሞ የፌደራል ፖሊሶች በንጹህ ኢትዮጵያውያን ላይ የወሰዱትን ኢ-ሰብአዊ ድርጊት በጽኑ አውግዟል። ገዢው ፓርቲ ለውስጥ ችግሩ ሰበብ መፈለጉን እንዲያቆም የታሰሩ አባሎቹም እንዲፈቱ ጠይቋል።