በአዲስ አበባ የቆሻሻ መጣያ ሰፈር በደረሰው አደጋ የሟቾች ቁጥር እያሻቀበ ነው

መጋቢት ፬ (አራት)ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በኮልፌ ቀራንዩ ወረዳ 01 በተለምዶ ቆሸ ሰፈር ተብሎ በሚታወቀው አካባቢ በተፈጠረው የቆሻሻ ክምር መደርመስ የሟቾች ቁጥር ከ50 በላይ የደረሰ ሲሆን፣ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች አሁንም እንደጠፉ መሆናቸውን ያነጋገርናቸው ሰዎች ገልጸዋል። አብዛኞቹ ሟቾች ሴቶችና ህጻናት ሲሆን፣ አስከሬን የመፈለጉ ስራ ቀጥሏል።
አስከሬን ሲያወጡ የነበሩ ወጣቶች እንደገለጹት ቁራን ሲቀሩ የነበሩ ህጻናት እንዲሁም፣ ከወለደች 3 ቀናት የሆናት እናት፣ ልጅና አባት በአደጋው ህይወታቸው አልፏል።
ጉዳቱ ከደረሰባቸው ሰዎች መካከል አንዷ የሆነችው ወ/ሮ ሙላቴ ለአሶሼትድ ኒውስ ስትገልጽ፣ “ መጀመሪያ ከባድና አስፈሪ ድምጽ ሰማሁ፣ ከዚያም ባለቤቴን ምን እንደተፈጠረ ጠየቅሁት፣ ከዚያም ድምጹ እየጨመረ መጣ፣ ከዚያም በፍጥነት ለመውጣት ሞከርኩ፣ ነገር ግን ቆሻሻው መሃል ላይ ያዘኝ፣ ከዚያ በሁዋላ ራሴን ሆስፒታል ውስጥ ነው ያገኘሁት። አሁን የልጆቼና የባለቤቴ እጣ ፋንታ ምን እንደሆነ አላውቅም” ብላለች።
አካል ጉዳተኛ ከሆነው ባሉዋ ጋር ጧፍ እና ሻማ በመሸጥ በአካባቢው ለ11 አመታት የኖረችው ወ/ሮ ሙላቴ፣ እግሮቼ ክፉኛ ተጎድተዋል። ከእንግዲህ እንደ ድሮው እሄዳለሁ ብዬ አላስብም። አሁን ከሆስፒታሉ የአስቸኳይ ክፍል እንድወጣ ታዝዣለሁ፣ የት እንደምሄድ ግን አላውቅም” በማለት እያለቀሰች መናገሩዋን የዜና ድርጅቱ ገልጿል።
አንድ ባልና ሚስት ደግሞ ምሽት ላይ የ12 እና 13 አመት ሁለት ታዳጊ ልጆቻቸውን አስተኝተው ለቅሶ ቤት ሄደው ሲመለሱ፣ ቤታቸው በናዳው ተውጡ፣ ሁለቱም ልጆቻቸው በተኙበት ህይወታቸው አልፎ አግኝተውታል። የአንደኛው አስከሬን በፍለጋ ሲገኝ፣ የሌላው ዜናውን እስካጠናከርንበት ሰአት ድረስ አልተገኘም። አባትና እናት ራሳቸውን ስተው በመውደቃቸው፣ ሁለቱም በአሁኑ ሰአት ሆስፒታል የሚገኙ ሲሆን፣ በተለይ እናትየው አይናቸው ከመንከራተት ውጭ መናገር እንደማይችሉ ወንደማገኝ ጋሹ በስፍራው ያሉ ሰፈርተኞችን አነጋግሮ ዘግቧል።
ከዚህ ቀደም በአካባቢው ቆሻሻ መድፋት ቆሞ ወደ ሰንዳፋ እንዲዞር ተደርጎ የነበረ ሲሆን፣ የሰንዳፋ አርሶአደሮች ባሰሙት ተቃውሞ የተነሳ እንደገና ቆሻሻ መድፋት መጀመሩን የአካባቢው ነዋሪዎች ይገልጻሉ።
በአስከሬን ፍለጋው ላይ የተሰማሩ ወጣቶች በሚያዩት ነገር ስሜታቸውን መረበሹን ይናገራሉ። በወጣቶች ግምት እስከ 150 የሚሆኑ ሰዎች ህይወታቸውን ሊያጡ ይችላሉ። የአካባቢው ባለሀብቶች ተረባርበው ስካቫተር እና ማመላለሺያ መኪኖችን እንደሰጡም ይገልጻሉ።
በሌላ በኩል አዲስ አበባ የሚገኘው የጀርመን ኢምባሲ፣ በደረሰው ጉዳት የተሰማውን ሀዘን ገልጾ፣ የአገሪቱና የአውሮፓ ህብረት ሰንደቅ አላማዎች ዝቅ ብሎ እንዲውለበለብ አድርጓል።