ኢሳት (መጋቢት 22 ፥ 2008)
በአዲስ አበባ የሚፈናቀሉ አርሶ አደሮችን ለማቋቋም የሚሰሩ ፕሮጄክት ጽ/ቤቶች ሊቋቋሙ እንደሆነ ተገለጸ።
ይህ የተገለጸው የአዲስ አበባ ሰራተኛ እና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ በረቂቅ ደንቡ ላይ የህዝብ ውይይት ለማድረግ በተጠራ ስብሰባ ላይ ሲሆን፣ በውይይቱ ላይ የሰራተኛ እና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ሃላፊ የሆኑት አቶ ኤፍሬም ግዛው እንደተናገሩት የፕሮጄክት ጽ/ቤት አላማ በልማት ተነሺ ሆነው በተለያዩ ምክንያቶች ለችግር የተጋለጡ አርሶ አደሮችን በጥናት የመለየትና መልሶ ማቋቋም ነው በማለት ተናግረዋል።
ለውይይት የቀረበው ረቂቅ ደንብ እንደሚያመለክተው ካሁን ቀደም በልማት ምክንያት ከይዞታቸው የተነሱና የተሰጣቸውንም ካሳ አሟጠው ተጠቅመው ለችግር የተጋጡ አርሶ አደሮችን በጥናት የመለየት መልሶ የማቋቋም ሃላፊነት ለፕሮጄክት ጽ/ቤት የተሰጠ ሃላፊነት እንደሆነ ይገልጻል።
በውይይቱ ላይ የተገኙት አርሶ አደሮች ከፍተኛ ምሬታቸውን ያሰሙ ሲሆን፣ “ውሻ ከሄደ ጅብ ጮኸ” በማለት ከዚሁ ቀደም የተሰጣቸው ካሳ በጣም አነስተኛና በጥቂት ጊዜያቶች አልቆ ለችግር መጋለጣቸውን አስታውሰዋል።
“እኛ ዘር እንጂ ብር የለንም፣ ወቅታዊውን የኢኮኖሚ ሁኔታ እና ዋጋ ያገናዘበ ካሳ አልተሰጠንም” በማለት መናገራቸውን የኢሳት ምንጮች ከአዲስ አበባ ገልጸዋል።
ከውይይቱ በኋላ ኢሳት ያነጋገራቸው የህብረተሰብ ክፍሎች እንደገለጹት ከሆነ፣ ረቂቅ ደንቡ በተግባር ላይ የማይውል ጊዜያዊ የፖለቲካ ትኩሳቱን ለማብረድ በማሰብ በግብታዊነት የተዘጋጀ መሆኑን አስታውቀዋል። በተለይም የተዘጋጀው ደንብ ወደኋላ ሄዶ ለችግር የተጋለጡ አርሶ አደሮችን ያቋቁማል መባሉ ተመልሶ የህዝብ ገንዘብ ወደ ባለስልጣናት ለመዝረፍ በማሰብ የተቀየሰ መሆኑን አስገንዝበዋል። ባለፉት ሃያ አመታት በአዲስ አበባ የተፈናቀሉ ከ150ሺህ በላይ አርሶ አደሮች የገቡበት ባልታወቀበት አብዛኞቹም ባጋጠማቸው ችግርና ብስጭት ምክንያት በህይወት በሌሉበት እንዲሁም ቤተሰብ ሙሉ ለሙሉ በተበተነበት ሁኔታ መልሶ ማቋቋም ይሰራል ማለት ወደ ተግባር የማይመነዘር ተራ ፕሮፓጋንዳ መሆኑን ገልጸዋል።
አስተያየት ሰጪዎች አያይዘውም እንደገለጹት መንግስት ለአርሶ አደሩ የሚያስብ ከሆነ መጀመሪያ በፌዴራል ፓርላማ የወጣውን ማለትም በምርጫ 97 ማግስት ሃምሌ 8 ቀን 1997 “የመሬት ይዞታ የሚለቀቅበትንና ለንብረት ካሳ የሚከፈለበትን ለመወሰን የወጣ አዋጅ በቅድሚያ መሰረዙን ለህዝብ ይፋ ማድረግ አለበት ብለዋል። በማስከተልም አዲሱ ደንብ “በአዲስ አበባ የልማት ተነሺ አርሶ አደሮችን ለማቋቋም” የሚለው በቀጣይነት የቀሩትን ገበሬዎች ሙሉ ለሙሉ ለማፈናቀል በማሰብ የተዘጋጀ መሆኑን አስገንዝበዋል።