በአዲስ አበባ የሚታየው የቆሻሻ ክምር እና ኮሌራ በነዋሪው ህዝብ ላይ ስጋት ፈጥሯል

ሐምሌ  ፳ ( ሀያ ) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- ዘጋቢያችን እንደገለጸው በከተማው የሚታዬው ቆሻሻ በነዋሪዎች ላይ ከፍተኛ ችግር እየፈጠረ ባለበት በዚህ ሰአት የኮሌራ በሽታ መስፋፋትና የንጹህ ውሃ አቅርቦት እጥረት መባባስ በነዋሪዎች ላይ ስጋት ደቅኗል።

በኦሮምያ ልዩ ዞን በርኬ ወረዳ የሚገኙ አርሶደሮች ሰንዳፋ አካባቢ በ337 ሚሊዮን ብር የተገነባው የ ቆሻሻ መጣያ  በጤናቸው ላይ ችግር እየፈጠረባቸው መሆኑን በመግለጽ፣ ከእንግዲህ በዚህ አካባቢ ቆሻሻ እንዳይጣል ማስጠንቀቃቸው ለቆሻሻው መጠራቀም ምክንያት ሆኗል። የአዲስ አበባ ነዋሪዎችም ሁኔታው ግራ እንዳጋባቸው ለኢሳት ወኪል ተናግረዋል

በሌላ በኩል በርካታ ዜጎች በኮሌራ በሽታ ተጠቅተው ህክምና እየተሰጣቸው ሲሆን፣ ሃኪሞቹ በበሽታው የተያዙ ሰዎችን የበሽታ አይነት ሲመዘግቡ ኮሌራ ብለው እንዳይሞሉ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷቸዋል። ስማቸው እንዳይገለጽ የፈለጉ ሃኪሞች፣   በኮሌራ በሽታ የተያዘ ሰው “ ሲቪላ ባክቴሪያ ታይት 2” እንደያዘው ተደርጎ  ሪፖርት እንዲደረግ ትእዛዝ እንደተሰጣቸው ተናግረዋል።

በሽታው ኮሌራ ተብሎ ሪፖርት ከተደረገ፣ ሪፖርት ያደረገው ባለሙያ እንደሚታሰር የገለጹት ሃኪሞች፣ ኮሌራ ገባ ከተባለ በቱሪዝምና በንግድ እንቅስቃሴው ላይ ከፍተኛ ተጽኖ ይኖረዋል ይላሉ። መንግስት መደበቅ የፈለገውም ከዚህ አንጻር ነው ሲሉ አክለዋል። የንጹህ ውሃ እጥረት ለበሽታው መስፋፋት ምክንያት መሆኑንም ባለሙያዎች ተናግረዋል።