ኢሳት (ሰኔ 23 ፥ 2008)
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በላፍቶ ከተማ ዙሪያ ህገወጥ ናቸው ያላቸውን የመኖሪያ ቤቶች ለማፍረስ እያካሄደ ባለው ዘመቻ ሃሙስ ተጨማሪ ሁለት ሰዎች በጸጥታ ሃይሎች ተገደሉ።
በዚሁ ክፍለ ከተማ ልዩ ስሙ ሃና ፋሪ ተብሎ በሚጠራው በዚሁ አካባቢ እየተካሄደ ባለው የመኖሪያ ቤቶችን የማፍረስ ሂደት ቁጥራቸው በአግባቡ ሊታወቅ ያልቻለ ነዋሪዎች ለእስር መዳረጋቸውን ለደህንነታቸው ሲሉ ስማቸውን መግለጽ ያልፈለጉ ነዋሪዎች ለኢሳት አስረድተዋል።
አዲስ ስታንዳርድ የተሰኘው መፅሄት በበኩሉ ረቡዕ ከሞቱ ሁለት ፖሊሶችና አንድ የወረዳ ስራ አስፈጻሚ በተጨማሪ አንድ ነዋሪ መገደሉን ሃሙስ ዘግቧል።
ለሁለተኛ ቀን ቀጥሎ ባለው የመኖሪያ ቤቶችን የማፍረስ ሂደት በርካታ የጸጥታ ሃይሎች ተሰማርተው በአካባቢው ከፍተኛ ቁጥጥርን እያደረጉ ሲሆን፣ የመገኛና ብዙሃን ወደስፍራው እንዳይዘልቁ መደረጉ ታውቋል።
ሃሙስ ረፋድ ላይ በጸጥታ ሃይሎች ከተገደሉ ሁለት ሰዎች መካከል አንደኛ በጥይት መገደሉንና ሌላ መንገደኛ በጸጥታ ሃይሎች ተደብድቦ ህይወቱ ማለፉን ነዋሪዎች ከዜና ክፍላችን ጋር ባደረጉት ቃለምልልስ አስረድተዋል።
የከተማዋ አስተዳደር ህገወጥ ግንባታ ታከሄዶበታል በሚለው የሃና ፋሪ አካባቢ ወደ 30ሺ የሚጠጉ ቤቶች ሲኖሩ አስተዳደሩ አብዛኞቹ መኖሪያ ቤቶች ህወገጥ እንደሆኑ ይገልጻል።
የመኖሪያ ቤታቸው እያፈረሰባቸው የሚገኘው ነዋሪዎች በበኩላቸው በአካባቢው ከ10 አመት በላይ መኖሪያቸውንና በዝናብ ወቅት የተጀመረው የማፍረስ ድርጊት አግባብ አለመሆኑን አስታውቀዋል።
ለደህንነታቸው ሲሉ አካባቢውን ለቀው እንደተሰደዱ የሚናገሩት ነዋሪዎች ቀርሳ ኮንቶማ ተብሎ በሚጠራው ስፍራ በርካታ ነዋሪዎች ድብደባ እየተፈጸመባቸው እንደሆነ ገልጸዋል።
የጸጥታ አባላት ገድለዋል የተባሉ ተጠርጣሪዎችን ለመያዝ እየተካሄደ ባለው ዘመቻ የጸጥታ ሃይሎች በነዋሪዎች ላይ እንግልት እየወሰዱ መሆናቸውም ታውቋል።
የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን በበኩሉ ረቡዕ በጸጥታ ሃይሎች ላይ ግድያን ፈጽመዋል የተባሉ ተጠርጣሪዎችን ለመያዝ ፍለጋን እያካሄደ እንደሆነ የገለጸ ሲሆን፣ ሃሙስ በተካሄደ የማፍረስ ዘመቻ በርካታ መኖሪያ ቤቶች እንዲፈርሱ መደረጉን ለመረዳት ተችሏል።
በሌሉበት የመኖሪያ ቤታቸው እንደፈረሰባቸው የተናገሩ ነዋሪዎች የከተማው አስተዳደር እንዲህ ያለ የሃይል እርምጃ መወሰዱ አግባብ አለመሆኑን ከሃገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን ተናግረዋል።
የከተማዋ አስተዳደር በተለያዩ ቦታዎች ህገወጥ ግንባታ ተካሄዶባቸው ያላቸውን የመኖሪያ አካባቢዎች ለማፍረስ በዝግጅት ላይ መሆኑን በድጋሚ ገልጿል።