በአዲስ አበባ ዙሪያ ባሉ የኦሮሚያ ከተሞች ተቃውሞ ተቀሰቀሰ

ኢሳት (መስከረም 24 ፥ 2009)

ማክሰኞ በአዲስ አበባ ከተማ አካባቢዎች የተጀመረው ተቃውሞ በዙሪያዋ ባሉ የኦሮሚያ ከተሞች መዛመቱን እማኞች ከኢሳት ጋር ባደረጉት ቃለ-ምልልስ አስታውቀዋል።

ማከሰኞች ረፋድ በከተማዋ ልዩ ስሙ ሞጆ መንደር እንዲሁም አየር ጤና አካባቢ ታይቶ የነበረው ተቃውሞ በቡራዩ አለም ገና እና በአቅራቢያ ባሉ አካባቢዎች ተባብሶ መቀጠሉን እማኞች ገልጸዋል።

በቡራዩ ከተማ የተጀመረውን ይህንኑ ተቃውሞ ተከትሎ ወደ ከተማዋ የሚወስዱ ዋና ዋና መንገዶች ዝግ መደረጋቸውንና በመንግስታዊ ተቋማት ላይ ጥቃት መፈጸሙን ለደህንነታቸው ሲሉ ስማቸውን መግለጽ ያልፈለጉ ነዋሪዎች አስረድተዋል።

ከቀናት በፊት በቢሾፍቱ ከተማ በመቶዎች ለሚቆጠሩ ሰዎች ሞት ምክንያት የሆነው የጸጥታ ሃይሎች ዕርምጃ ተቃውሞ እንዲቀሰቀስ አስተዋጽዖ ማድረጉን ከእማኞች ለመረዳት ተችሏል።

ህዝባዊ ተቃውሞውን ለመቆጣጠር በሚል የጸጥታ ሃይሎች የሃይል ዕርምጃን ለመውሰድ ቢሞክሩም ተቃውሞው ሊቆም አለመቻሉን የቡራዩ ከተማ ነዋሪዎች ገልጸዋል።

ለወራት በኦሮሚያ ክልል ሲካሄድ የቆየው ህዝባዊ ተቃውሞ ዳግም መቀስቀሱን የተናገሩት ነዋሪዎች በመዲናይቱ አዲስ አበባ በተለምዶ አየር ጤና ተብሎ በሚጠራ አካባቢ ተመሳሳይ ተቃውሞ ሲካሄድ ማምሸቱን በስፍራው የነበሩ እማኞች ለኢሳት አስረድተዋል።

በአካባቢው ያሉ የንግድ ድርጅቶችና በርካታ አገልግሎት መስጫ ተቋማት ዝግ ሆነው መዋላቸውን የሚናገሩት ነዋሪዎች፣ ትምህርት ቤቶች ጭምር ተዘግተው እንደነበረም አስታውቀዋል።

ማክሰኞ በአዲስ አበባ አንዳንድ ቦታዎች ተስተውሏል የተባለው ተቃውሞና ግርግር ነዋሪዎች ዘንድ ስጋት ማሳደሩም ተነግሯል።

የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን በበኩሉ በከተማዋ አንዳንድ አካባቢዎች ሁለት ለማስፋፋት ጥረት ተደርጓል ሲሉ ድርጊቱን አስተባብሏል።

የኮሚሽኑ ዋና አዛዥ አቶ አሰፋ አብዩ ከውጭ ሃይሎች ትዕዛዝ ተቀብለዋል ሲሉ የገለጿቸው አካላት በእንቅስቃሴው ተሳታፊ እንደነበሩ ለሃገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን ተናግረዋል።

ይሁንና ፖሊስ ኮሚሽን በመዲናይቱ ተፈጥሯል የተባለውን ድርጊት ቢያረጋግጥም በጉዳዩ ዙሪያ ዝርዝር መረጃን ከመስጠት ተቆጥበዋል።