መስከረም ፳፬ (ሃያ አራት) ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በአዲስ አበባና በዙሪያዋ በሚገኙ ከተሞች በአየር ጤና ፣ ጆሞ፣ አስኮ ፣ ቡራዩ፣ ሰበታ፣ ኮልፌ፣ በአለም ገና፣ አቃቂ ቃሊቲ እና ሌሎችም አካባቢዎች ህዝባዊ ተቃውሞ ሲካሄድ ውሎአል። በርካታ ንብረት ወድሟል። የንግድ ድርጅቶች ተዘግተዋል። ተሽከርካሪዎች እንቅስቃሴ አቁመዋል። መርካቶ የሚገኙ ሱቆችና ሆቴሎች ተዘግተዋል።
ቡሌቦራ ከተማም እንዲሁ ከፍተኛ ተቃውሞ ሲካሄድ የዋለ ሲሆን የትናንትናውን ጨምሮ 2 ሰዎች ተገድለዋል። በገረባ ከተማም እንዲሁ 4 ሰዎች መሞታቸውን የአካባቢው ነዋሪዎች ተናግረዋል። በርካታ የመንግስት መስሪያ ቤቶች ወድመዋል።
በደቡብ ክልል የሚታየው ውጥረት እየጨመረ መምጣቱንም ከስፍራው የደረሰን መረጃ ያመለክታል።
በኤሪቻ በአል ላይ የተገደሉት ዜጎችን ለመፈለግ ወዳጅ ዘመዶች ጥረታቸውን ቀጥለዋል። አስከሬናቸው የተገኙ ዜጎች በተለያዩ የክልሉ ከተሞች ቀብራቸው እየተፈጸመ ሲሆን፣ ቤተሰቦቻቸውን በግፍ የተነጠቁ ቤተሰቦች አዘናቸውን ገልጸዋል።