በአዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽ ባለስልጣን መስሪያ ቤት ውስጥ የሚታየው የንብረት ውድመትና ሙስና አስከፊ ነው ተባለ

መስከረም ፳፪(ሃያ ሁለት)ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- ከፍተኛ ገንዘብ ወጥቶባቸው በተዝረከረከ የንብረት አስተዳደር ሥርዓት ምክንያት ለብክነት፣ ለምዝበራ እና ለብልሽት የተጋለጡ ንብረቶችን ለመታደግ ትክክለኛ የአሰራር ስርዓት መጥፋቱን፣ የመስሪያ ቤቱ ባለስልጣናትም ያለጠያቂ በሙስና መዘፈቃቸውን  የፌድራል የስነ ምግባር እና የጸረ ሙስና ኮሚሺን ገለጸ፡፡

በአዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽ ባለስልጣን ውስጥ የDCI እና የDN  የቧንቧ መገጣጠሚያዎች ቁመታቸው እና ውፍረታቸው በናሙና እየተለካ ሌሎች መመዘኛዎች ግን በአብዛኛው በእይታ እየተረጋገጡ ገቢ እንደሚደረጉና በዚህም የተነሳ ስራ ላይ ሲውሉ የጥራት ችግሮች እንደሚያጋጥማቸው ለመረዳት ተችሏል፡፡

ክሊች፣ submersible pump የሚባሉ እቃዎች ተገዝተው ገቢ ከሆኑ በኋላ ለስራው የማያገለግሉ መሆናቸውን በመረጋገጡ ከ 92 ሚልየን ብርበላይ የህዝብ ሃበት ሜዳ ላይ ፈሶ እንዲቀር መደረጉን ለማወቅ ተችሎአል።

የእቃዎች ገቢ ማድረጊያ ሠነድ የተሟላ ካለመሆኑ በተጨማሪ ሠነዱን በአግባቡ አለመሞላትና ንብረቶቹ የገቢ ሰነድ ሳይሰራላቸው ለረጅም ጊዜ የመቆየታቸው ሁኔታ ፀረ ሙስና የለያቸው ችግሮች ናቸው፡፡

በአዲስ አበባ ውሃ ሥራዎች ባለስልጣን ንብረቶች በእቃ ግምጃ ቤት ውስጥ የጥራት ደረጃ ያሟሉ መሆን አለመሆናቸው ሳይረጋገጥ እና የገቢ ሰነድ ሳይሰራላቸው ለረጅም ጊዜ ተከማችተው እንደሚገኙ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስም የማረጋገጥ ስራ ያልተሰራላቸው ነገር ግን ከ90 በመቶ በላይ ክፍያ የተፈፀመባቸው እቃዎች መኖራቸውን ጸረ ሙስና አረጋግጧል፡፡

GW1 እየተባለ በሚጠራው የእቃ ግምጃ ቤት ከ 2 እስከ 4 ኢንች የሆኑ 1 ሺ 516 የውሃ ቆጣሪዎች፣ በቀድሞ ዋና መ/ቤት የቴክኒክ እቃዎች የእቃ ግምጃ ቤት ውስጥ ግማሽ ኢንች 3 ሺ ፣ ሶስት ኢንች 5 ሺ የውኃ ቆጣሪዎች፣ እና በርካታ ንብረቶች ተከማችተው መኖራቸውና በእቃ ግምጃ ቤት ውስጥ የሚገኙ የተለያየ ብዛት እና መጠን ያላቸው እቃዎችን በወቅቱ የጥራት ቁጥጥር ሳይደረግባቸው፣ የገቢ ሰነድ ሳይሰራላቸው በንብረትነት ሳይያዙ፣ ለረጅም ጊዜ መቆየታቸው ለሙስናና ብልሹ አሰራር የሚያጋልጥ ሁኔታ እንዳለ በግልፅ ማሳየቱን ኮሚሽኑ አመልክቷል።

በ1995 ዓ.ም የተገዙ 255 ሺ የኤቢሲ ኬብል ፣ 74 ሺ የ20 ኬብል፣ 25,ሺ 30 ኪብል ስራ ላይ ያልዋሉ ሲሆን ፣ ለፀሃይና ዝናብ ተጋልጠው እየተበላሹ ካሉት መካከል ደግሞ  በ2000 ዓ.ም የተገዙ 106 ሺ 275 ፒን ቦልትድ

፣ በ2001 ዓ.ም የተገዛ  ባለ 6 ሚ.ሜ 1 ሚሊየን 285 ሺ 200 ሜትር ሽቦ፣  እና በሺዎች የሚቆጠሩ ቆጣሪዎች ስራ ላይ ያልዋሉ መሆኑ ተመልክቷል።

በጥናቱ የተለየው ሌላው ችግር የንብረት አስተዳደር አሰራር ንብረቶችን በአግባቡ ለማስተዳደር እና ለመቆጣጠር በማያስችል ሁኔታ ላይ ያለ በመሆኑ እቃዎች ለስርቆት፣ ለብልሽት እና ለቃጠሎ ተዳርገዋል የሚል ነው፡፡ ይህ ችግር የሚታየው በተለይ በአዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽ ባለስልጣን ሲሆን ንብረቶቹ እጅግ በተራራቁ እና ለመቆጣጠር በማያስችል ሁኔታ በአንድ የእቃ ግምጃ ቤት ባለሙያ ሃላፊነት እንዲያዙ በመደረጉ በሰው እና በተፈጥሮ ሁኔታ ማለትም በዝናብ እና በፀሐይ ንብረቶች እንዲበላሹና እንዲሰረቁ፣ በዚህም የተነሳ ስራ ላይ ሲውሉ ከፍተኛ የውሃ ብክነትን እንዲያስከትሉ፣ ከወጣባቸው የገንዘብ መጠን አኳያ ተመጣጣኝ አገልግሎት እንዳይሰጡ በማድረግ ተቋሙን ላላስፈላጊ ግዥዎች ዳርገውታል፡፡

በሪፖርቱ በርካታ የአሰራር ግድፈቶችና ሙስኒአ ተፈጸመባቸው ዝርዝሮች የቀረቡ ሲሆን መስሪያ ቤቱ በአሰራር ችግርና በንብረት ቁጥጥር ማነስ ከ1 ቢሊዮን 900 ሚሊዮን ብር በላይ ንብረት እንዲባክን ማድረጉ ተጠቅሷል።