ጥቅምት ፳(ሃያ) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-በአዲስአበባ የመኖሪያ ቤቶችን እጥረትን ለመፍታት ዳግም በተደረገው ምዝገባ ከ993 ሺ በላይ ቤት ፈላጊዎች መመዝገባቸውንና ይህን የቤት ፍላጎት ለማርካት በመንግስት በኩል እየተካሄዱ ያሉ ግንባታዎች አፈጻጸም ደካማ
መሆኑን ከኢትዮጵያ የኮንስትራክሽን ፕሮጀክት ማኔጅመንት ኢንስቲትዩት የተገኘ መረጃ ጠቁሟል። እንደመረጃው ከሆነ የአዲስአበባ ቤቶች ግንባታ ለማየት በተካሄደው የመስክ ግምገማ የአዲስአበባ
የቤቶች ግንባታ አፈጻጸም በዝቅተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል ፡፡ በቤቶች ግንባታው ዘርፍ ከሚታዩት ችግሮች ቀዳሚው የአቅም ማነስ ሲሆን የማቴሪያል አቅርቦት ችግር እንዲሁም ሙስናና ብክነት ተጠቅሰዋል።
በ2006 ዓ.ም ብቻ አስተዳደሩ ከ11 ቢሊየን ብር በላይ ለቤቶች ግንባታ መድቦ ግንባታ እያከናወነ ቢሆንም ሥራዎችን በፍጥነትና በጥራት ከማከናወን አኩዋያ ድክመቶች በመኖራቸው የነዋሪውን ፍላጎት ማርካት ካለመቻሉም በላይ ነዋሪው በአስተዳደሩ ስራ ላይ ተስፋ እንዲቆርጥ ምክንያት ሆኗል፡፡ አስተዳደሩ በከተማዋ ያለውን
የቤት ችግር ለመቅረፍ በዓመት 50 ሺ ቤቶችን ለመገንባት ያቀደ ሲሆን በአሁኑ ወቅት የመገንባት አቅሙ በዓመት በአማካይ ከ12 ሺ ቤቶች በላይ የዘለለ አለመሆኑ በየዓመቱ እያደገ የሚመጣውን የቤትv ፍላጎት በአግባቡ ለመመለስ ጨርሶ እንደማያስችለው ታውቋል፡፡
አስተዳደሩ በሚቀጥሉት ሶስት ወራት ጊዜ ውስጥ የ20 በ80 ኮንዶሚኒየም ቤቶችን በዕጣ ፣ የ10 በ90 ስቱዲዮ ቤቶች ሙሉ በሙሉ እንዲሁም የ40 በ60 ቤቶችን ሙሉ ክፍያ ለሚፈጽሙ ለማስተላለፍ ዕቅድ የያዘ ሲሆን ኢህአዴግ
መራሹ መንግስት ይህን ሥራ ምርጫው ወደሚቃረብበት ወራት የገፋው ግንባታውን እንደድጋፍ ማሰባሰቢያ ሊጠቀምበት አቅዶ ሊሆን እንደሚችል ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ወገኖች ጠቁመዋል፡፡
መንግስት የነዋሪው የቤት ፍላጎት መጨምርን ተከትሎ እስከዛሬ ሲከተለው የነበረውን ፖሊሲ በመቀየር የውጭ አገር ባለሃብቶች በቤት ግንባታ እንዲሳተፉ ፈቃድ ሰጥቷል።
የአገር ውስጥ ተቋራጭ ድርጅቶች አቅም መዳከም የውጭ አገር ድርጅቶችን ለመጋበዝ መገደዱን መንግስት ቢያስታውቅም፣ ሌሎች ወገኖች ግን መንግስት የቤቶችን ግንባታ ለማከናወን የገንዘብ አቅም ስላጋጠመው የውጭ ድርጅቶችን ለመጋበዝ ፈቅዳል ይላሉ።