ኢሳት (ግንቦት 18 ፥ 2008)
ሰሞኑን በአዲስ አበባ ቦሌ ክፍለ ከተማ ልዩ ስሙ ወረገኑ ተብሎ በሚጠራ አካባቢ ህገወጥ ናቸው የተባሉ የመኖሪያ ቤቶችን የማፍረሱ እርምጃ ሃሙስም ለሁለተኛ ሳምንት ጊዜ ቀጥሎ ተጨማሪ አንድ ሰው መሞቱን እማኞች ለኢሳት ገለጹ።
ለደህንነታቸው ሲሉ ስማቸውን መናገር ያልፈለጉት ነዋሪዎች የጸጥታ ሃይሎች አሁንም ድረስ በአካባቢው በመስፈር በነዋሪዎች ላይ እርምጃን እየወሰዱ መሆኑን አስታውቀዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ወረገኑ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ወደ ሁለት ሺ የሚጠጉ የመኖሪያ ቤቶች ህገወጥ ተብለው መፈረጃቸውንና የማፍረሱ ድርጊትም ወረገኑን ጨምሮ በሌሎች አካባቢዎችም እንደሚካሄድ ገልጿል።
በወረገኑ መንደር ከ30 ሺ የሚበልጥ ሰው በመኖር ላይ መሆኑን የተናገሩት የአካባቢው ነዋሪዎች የጸጥታ ሃይሎች ከአፍራሽ ግብረ ሃይል ጋር በመሆን በነዋሪዎች ላይ የሃይል እርምጃን እየወሰዱ እንደሆነ ከዜና ክፍላችን ጋር ባደረጉት ቃለምልልስ አስረድተዋል።
በጸጥታ ሃይሎች በተወሰደ እርምጃ ሃሙስ የተፈጸመውን ግድያ ጨምሮ ከ10 የሚበልጡ ነዋሪዎች መገደላቸውን በሃገር ውስጥ ያሉ መገናኛ ብዙሃን ጨምሮ የተለያዩ አካላትን ዋቢ በማድረግ ዘግበዋል።
በጉዳዩ ዙሪያ ዝርዝር መረጃን ከመስጠት ተቆጥቦ የሚገኘው የከተማዋ አስተዳደር በበኩሉ በጸጥታ ሃይሎች ላይ ሁከትን ፈጥረዋል የተባሉ ቁጥራቸው ያልተገለጸ ነዋሪዎች ለእስር መዳረጋቸውን ለመንግስት መገናኛ ብዙሃን ገልጸዋል።
ያለ ምንም መጠለያ ተቸግረው እንደሚገኙ የተናገሩት ነዋሪዎች በርካታ ሰዎች ወደዘመድ ጋር ለመጠጋት ከአዲስ አበባ ከተማ ውጭ በመጓዝ ላይ መሆናቸውንም አስታውቀዋል።
በወረገኑ መንደር ተሰርተው የነበሩ ትምህርት ቤቶች ጭምር በመፍረስ ላይ መሆናቸው ህጻናት ያለ ትምህርት ቀርተውብናል ሲሉ ነዋሪዎቹ ቅሬታቸውን በመግለጽ ላይ ሲሆኑ፣ የከተማዋ አስተዳደር በበኩሉ በአካባቢው የጎልፍ መጫወቻና ሌሎች ግንባታዎች እንደሚካሄዱበት ይፋ አድርጓል።
በከተማዋ ወረዳ 12 ልዩ ስሙ ወረገኑ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ እየተካሄደ ያለው እርምጃም በቅርቡ በወረዳ 11 እና 10 እንደሚቀጥል የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አስታውቀዋል።
በሺዎች የሚቆጠሩ ተጨማሪ ነዋሪዎች ከመኖሪያ ቀያቸው ሊፈናቀሉ ይችላል ተብሎ መሰጋቱን ከሃገር ቤት ከተገኘ መረጃ ለመረዳት ተችሏል።