በአዲስ አበባ ከፍተኛ የጸጥታ ቁጥጥር በመካሄድ ላይ መሆኑን ነዋሪዎች ገለጹ

ኢሳት (ጥር 15 ፥ 2009)

የአፍሪካ ህብረት ጉባዔ በአዲስ አበባ ከተማ መጀመሩን ተከልትሎ በከተማዋ ፍተሻን ጨምሮ የጸጥታ ቁጥጥር በመካሄድ ላይ መሆኑንም ነዋሪዎች ገለጹ።

ልዩ ጉባዔው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ተግባራዊ ተደርጎ ባለበት ወቅት የሚካሄድ በመሆኑ የፌዴራልና የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ከመቼውም ጌዜ በላይ የተጠናከረ የጸጥታ ቁጥጥር መጀመሩን ከሃገር ቤት የተገኘ መረጃ አመልክቷል።

በመዲናይቱ አዲስ አበባ ተሽከርካሪዎችን በማስቆም ፍተሻ በመካሄድ ላይ መሆኑን የተናገሩት ነዋሪዎች ተሰባስበው የሚታዩ ሰዎች በጸጥታ ሃይሎች እንደሚዋከቡም አስረድተዋል።

በሃገሪቱ ተግባራዊ የተደረገን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ተከትሎ የአፍሪካ ህብረት ልዩ ጉባዔውን በአዲስ አበባ ለማካሄድ ስጋት እንዳደረበት ሲገልፅ መቆየቱ ይታወሳል።

ህብረቱ ያቀረበውን ይህኑ ስጋት ተከትሎ የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሃላፊዎች ከአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ተወካዮች ጋር በተደጋጋሚ ምክክር ሲያካሄዱ ቆይተዋል።

መንግስት ጉባኤው በተያዘለት እቅድ መሰረት እንዲካሄድ ማረጋገጫ በመስጠቱ ምክንያት የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባዔ  በአዲስ አበባ እንዲካሄድ መወሰኑን አፍሪካ ኒውስ በቅርቡ ዘግቧል።

የህብረቱ አባል ሃገራት አምባሳደሮች ለዚሁ ልዩ የመሪዎች ጉባዔ የሚቀርብ አጀንዳ ላይ ትናንት እሁድ በህብረቱ ዋና ጽ/ቤት ስብሰባ መጀመራቸውን የህብረቱ መረጃ ያመለክታል።

በቀጣይ ቀናቶች የህብረቱ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮችን ጨምሮ የተለያዩ ሃገራት ተወካዮች ወደ አዲስ አበባ ይገባሉ ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን፣ የጸጥታ ቁጥሩም በርካታ የሲቪልና መደበኛ የጸጥታ አባላት አካቶ በመሄድ ላይ መሆኑን ለመረዳት ተችሏል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በበኩሉ የከተማዋ ነዋሪዎች የህብረቱ ልዩ ጉባዔ ተጀምሮ እስከሚጠናቀቅ ድረስ ህብረተሰቡ ትብብር እንደሚያደርግ ጥሪውን አቅርቧል።

የህብረቱ ልዩ ጉባዔ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በታወጀበት አባል ሃገር ሲካሄድ ለመጀመሪያ ጊዜ መሆኑም ይነገራል።

መንግስት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መቼ እንደሚነሳ ቢጠየቅም አዋጁን ለማንሳት የተገኙ ውጤቶችን መገምገም ያስፈልጋል በማለት ምላሽን የሰጠ ሲሆን፣ አሜሪካና ብሪታኒያ በአዋጁ ምክንያት ዜጎቻቸው ወደ ኢትዮጵያ በሚያደርጉት ጉዞ ላይ ጥንቃቄን እንዲያደርጉ አሳስበው ይገኛል።