በአዲስ አበባ ከተማ የሚገኙ የውጭ ሃገራት ተወካዮች መንግስት የተቋረጠውን የኢንተርኔት አገልግሎት አለማስጀመሩ በስራቸው ላይ ችግር እየፈጠረ ነው አሉ

ኢሳት (ጥቅምት 3 ፥ 2008)

መቀመጫውን በአዲስ አበባ ከተማ ያደረጉ የውጭ ሃገራት ተወካዮች መንግስት የተቋረጠውን የኢንተርኔት አገልግሎት አለማስጀመሩ በስራቸው ላይ ችግር መፍጠሩን ገለጡ።

ረቡዕ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባለስልጣናት ጋር ተግባራዊ ተደርጎ በሚገኘው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ዙሪያ ውይይትን ያካሄዱ አምባሳደሮች የኢንተርኔት አገልግሎት መቼ እንደሚቀጥል ማረጋገጫ እንዲሰጣቸው ጥያቄ ማቅረባቸው ታውቋል።

ይሁንንና የመንግስት ባለስልጣናት አገልግሎቱ መቼ እንደሚጀምር ማረጋገጫ አለመሰጠቱ ስጋት እንደሆነባቸው በኢትጵያ የዴንማርክ አምባሳደር ሜቴ ታይግሰን መግለጻቸውን አፍሪካ ኒውስ ሃሙስ ዘግቧል።

በቢሾፍቱ ከተማ ከሬቻ በዓል አከባበር ጋር በተያያዘ የተፈጸመውን ዕልቂት ተከትሎ በተለያዩ የኦሮሚያ ከተሞች ህዝባዊ ተቃውሞዎች መቀስቀሱ ይታወሳል። ይሁንና መንግስት ድርጊቱን ለመቆጣጠር በሚል በመደበኛ በተንቀሳቃሽ ስልኮች ላይ የኢንተርኔት አገልግሎት እንዲቋረጥ ማድረጉ ይታወሳል።

በአንድዳንድ አካባቢዎች በመደበኛ ስልኮች ላይ የኢንተርኔት አገልግሎት ቢቀጥልም፣ በተንቀሳቃሽ ስልኮች ላይ ግን እገዳው አለመነሳቱን የዜና ወኪሉ አመልክቷል።

በዚሁ አገልግሎት መቋረጥ ቅሬታቸውን ያቀረቡ የተለያዩ ሃገራት አምባሳሰሮች ተወካዮች ችግሩ ዕልባት እንዲያገኝ ሲሉ ጥያቄን አቅርበዋል።

ከሃገራት ተወካዮች በተጨማሪ የአውሮፓ ህብረትና የተባበሩት መንግስታት ድርጅት መንግስት ያቋረጠውን የኢንተርኔት አገልግሎት እንዲጀመር ጥሪ ማቅረባቸውን የአፍሪካ ኒውስ ዘግቧል።

በተለያዩ ሃገራት በመካሄድ ላይ ያለው ህዝባዊ ተቃውሞ ዕልባትን እስኪያገኝ ድረስ አገልግሎት ተቋርጦ እንደሚቀጥል መንግስት በተደጋጋሚ ሲገልጽ የቆየ ሲሆን፣ በአስችኳይ የጊዜ አዋጁ ደንብ የኢንተርኔት አገልግሎት ትኩረት እንደተሰጠው ታውቋል።

የአገልግሎቱ ተጠቃሚዎች ካለፈው ወር ጀምሮ የተለያዩ ድረገጾችን መጠቀም እንዳልቻሉ በመግለጽ ላይ ናቸው።