በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሹም ሽሩ ቀጥሏል

ኢሳት ዜና (መስከረም 12 ፣ 2008)

በቅርቡ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ውስጥ በሚገኙ 4ሺ በላይ የመንግስት ሰራተኞች ላይ እርምጃ የወሰደው የከተማዋ አስተዳደር በአስር ክፍለ ከተሞች ሹምሽር አካሄዷል።

ከቀናት በፊት በተጀመረው በዚሁ ሹም ሽር በ116 ወረዳዎች የሚገኙ ከ100 በላይ አመራሮች የተነሱ ሲሆን የከተማዋ አስተዳደር ድርጊቱ ከትምህርት ብቃት ጋር የተገናኘ እንደሆነ መግለፁን ከሃገር ቤት የተገኘ መረጃ አመልክቷል። በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክ/ከተማ ብቻ ከዲፕሎማ በታች የትምህርት ደረጃ አላቸው የተባሉ አመራሮች ከሃላፊነታቸው መነሳታቸውን ያስታወቀው የከተማዋ አስተዳደር፣ 30 ተጨማሪ አመራሮችን ደግሞ ከሙስና ጋር በተገኛኘ ከስራቸው እንዲነሱ መደረጉን ይፋ አድርጓል።

በትምህርት ደረጃ ከስራቸው ተነስተዋል የተባሉ አመራሮች በበኩላቸው፣ አስተዳደሩ የወሰደው እርምጃ ፍትሃዊ እንዳልሆነ በመግለጽ ላይ መሆናቸውን በሃገር ውስጥ ያሉ መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።

ከአንድ ወር በፊት የከተማዋ አስተዳደር በአዲስ አበባ ከተማ በሚገኙ የመንግስት መስሪያ ቤቶች ላይ አስተዳደራዊና የሙስና ችግር አካሄደዋል ባላቸው ከ አራት ሺ በላይ ሰራተኞች ላይ እርምጃ መውሰዱን መግለጹ ይታወሳል።

ከቀናት በፊት ለሁለተኛ ጊዜ የተካሄደው የሹም ሽር እርምጃም አስተዳደሩ ከወሰዳቸው ውሳኔዎች መካከል ዋነኛው ሲሆን በመቶዎች የሚቆጠሩ አመራሮች ከሃላፊነታቸው እንዲነሱ ተደርገዋል።

የመሬት የሊዝ ጨረታዎችና የንግድ ፈቃስድ አሰጣጦች በከተማዋ አስተዳደር ሙስና ከተንሰራፋባቸው ዘርፎች መካከል ዋነኞቹ ሲሆኑ የተጀመረው የሹም ሽር እርምጃ፣ በክልሎችም ተግባራዊ ይደረጋል ተብሎ ይጠበቃል።

ሹም ሽሩ በርካታ አመራሮችን ከአዲስ አበባ ከተማ ካቢኔ አባልነት የሚያስወጣ እንደሆነና በምትካቸው አዳዲስ የካቢኔ አባላት እንደሚሾሙ ታውቋል።