(ኢሳት ዲሲ–የካቲት 26/2011) በአዲስ አበባ ከተማ በ8 ቡድኖች ተደራጅተው በጦር መሳሪያ የተደገፈ ከባድ የወንጀል ድርጊቶችን ሲፈፅሙ የነበሩ 48 ተጠርጣሪዎች መታሰራቸውኝ የከተማዋ ፓሊስ ኮሚሽን አስታወቀ፡፡
ኮሚሽኑ በአዲስ አበባ በተለይም በኮልፌ ቀራንዮ፣ በንፋስ ስልክ ላፍቶ፣ በየካ፣ ቦሌ እንዲሁም በአዲስ አበባ ዙሪያ ኦሮሚያ ልዩ ዞን በቡራዩ፣ በሰበታና በሆለታ አካባቢ በሌሊት ዘረፋ እየተስፋፋ መምጣቱን ይፋ አድርጓል፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ በውጭ ሀገር ዜጎች፣ በባለሀብቶችና በመንግስት መሰረተ ልማቶች ላይ ያነጣጠረ ዘረፋ እና የተደራጀ የከባድ ወንጀል ድርጊቶች እንደተደጋገሙ በመፈጸም ላይ መሆናቸውን የከተማዋ ፖሊስ አስታውቋል፡፡
ፖሊስ እንዳለው በአዲስ አበባና አካባቢዋ ለሁለት ወራት በተደረገ ጥናትና ክትትል በስምንት የተለያዩ ቡድኖች ወስጥ የተደራጁ 48 ተጠርጣሪዎችና የወንጀል ፍሬ የሆኑ ኤግዚቢቶች በቁጥጥር ስር ውለዋል፡፡
ተጠረጣሪዎቹ በፈፀሙት የወንጀል ድርጊቶች የዘርፏቸው ሽጉጦች፣ ተሽከርካሪዎች፣ በርካታ የኢትዮጵያና የውጭ ሀገር ገንዘቦች በቁጥጥር ስር እንደዋሉ በኮሚሽኑ የወንጀልና ትራፊክ አደጋ ምርመራፍል አስታውቋል፡፡
በአዲስ አበባ በተለይም በኮልፌ ቀራንዮ፣ በንፋስ ስልክ ላፍቶ፣ በየካ፣ ቦሌ እንዲሁም በአዲስ አበባ ዙሪያ ኦሮሚያ ልዩ ዞን በቡራዩ፣ በሰበታና በሆለታ አካባቢ በሌሊት ዘረፋ እየተስፋፋ መምጣቱን ፖሊስ ይፋ አድርጓል፡፡
ተጠርጣሪዎቹን ለመያዝ ፖሊስ ያደረገውን ብርቱ ጥረት በመደገፍ ብሔራዊ የመረጃና ደህንነት አገልግሎት፣ በሀገር መከላከያ ሠራዊት የደቡብ ዕዝና የመረጃ መምሪያ፣ የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስና ሌሎች የፀጥታ አካላት ከፍተኛ ተሳትፎ ነበራቸው ተብሏል፡፡
ይህን ስራ ለውጤት በማብቃት ከፍተኛ ተግባር ላከናወኑ የምርመራና ክትትል ቡድኑ አባላትና ጥቆማ በመስጠት ተሳትፎ ለነበራቸው የከተማዋ ነዋሪዎችም ፖሊስ ምስጋና አቅርቧልል፡፡