ኢሳት (መጋቢት 5 ፥2009)
በአዲስ አበባ ከተማ በተለምዶ ቆሼ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ከቀናት በፊት ከደረሰው አደጋ የተረፉ በርካታ ሰዎች የጠፉ ሰዎችን የማፈላለጉ ስራ ተጓትቷል በማለት ቅሬታ ማቅረብ ጀመሩ።
ቅሬታ አቅራቢዎቹ አሁንም ድረስ ከፍራሹ ሊወጡ ያልቻሉ ሰዎች መኖራቸውንና ፍለጋው ከተጠበቀው በላይ መጓተት ማሳየቱን እንደገለጹ ቪኦኤ የእንግሊዝኛው ክፍል ቅሬታ አቅራቢዎችን ዋቢ በማድረግ ማክሰኞ ዘግቧል።
“በአግባቡ የሚረዳን አካል ባለመኖሩ እራሳችን የቁፋሮ ስራ እያከናወንን ነው” ሲሉ አቶ ካሌብ ጸጋዬ የተባሉና የቤተሰብ አባላቸውን ማግኘት ያልቻሉ የአካባቢው ነዋሪ ገልጸዋል።
ማክሰኞ በተካሄደ የፍለጋ ስራ ተጨማሪ አስከሬን በመገኘቱ የሟቾች ቁጥር 72 የደረሰ ሲሆን፣ አሁንም ድረስ የቤተሰብ አባሎቻቸውን እጣ ፈንታ ማወቅ ያልቻሉ ሰዎች በግል ጭምር ቁፋሮ መጀመራቸው ታውቋል።
መንግስት እያካሄደ ያለው የነፍስ አድን ስራም እጅግ የተጓትተና አሳፋሪ ነው ሲሉም ቅሬታ አቅራቢዎቹ ለዜና አውታሩ አስረድተዋል።
በመንግስት በኩል ቸልተኝነት ታይቷል የሚሉት ከአደጋው የተረፉ ነዋሪዎች አስፈላጊው ድጋፍ በወቅቱና በፍጥነት ቢካሄድ ኖሮ የሰው ህይወት ሊተርፍ እንደሚችል አክለው አስታውቀዋል።
አምነስቲ ኢንተርናሽናልን ጨምሮ የተለያዩ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ተቋማትና ግለሰቦች በበኩላቸው መንግስት ለደረሰው አደጋ ሃላፊነት መውሰድ ይኖርበታል ብለዋል። በርካታ ነዋሪዎች በዚሁ አስከፊ ሁኔታ ውስጥ ሲኖሩ መንግስት ነዋሪዎችን ከስፍራው ማራቅ እንደነበረበት እነዚሁ አካላት ተናግረዋል።