በአዲስ አበባ ከመሬታቸው የተፈናቀሉ አርሶ አደሮች የከተማው አስተዳደር ካሳ እንዲከፍላቸው ጠየቁ

ኢሳት (ታህሳስ 17 ፥ 2009)

በአዲስ አበባ ከተማ ዙሪያ ለልማት ተብሎ ከእርሻ መሬታቸው የተፈናቀሉ አርሶ አደሮች የተወሰደባቸው መሬት ለአመታት ታጥሮ ያለምንም አገልግሎት በመዋሉ የከተማው አስተዳደር ኪሳራውን አስልቶ ካሳ እንዲከፍላቸው ጠየቁ።

እነዚሁ ከ1988 ጀምሮ መሬታቸው ለልማት ተብሎ የተወሰደባቸው አርሶ አደሮች በመፈናቀላቸው ምክንያት ሃብትና ንብረት አልባ ሆነው ሲቀመጡ የተባለው የህዝብ ጥቅም ሳይከበር የታለመው ልማትም ሳይመጣ መሬቱ ታጥሮ ያለስራ መቀመጡ እንዳስቆጫቸው ገልጸዋል።

በተወካዮቻቸው በኩል ለከንቲባ ድሪባ ኩማ ጥያቄያቸውን ያቀረቡት አርሶ አደሮች ታጥረው የተቀመጡ ቦታዎች ላይ የነበሩ አርሶ አደሮች እስካሁን ድረስ መሬታቸውን ቢያለሙ ሊያገኙ የሚችሉትን ሃብት መንግስት በቅጣት መልክ መሬቱን ከወሰዱ አካላት ተቀብሎ እንዲከፈላቸው መጠየቃቸውን በሃገር ውስጥ ያሉ መገኛኛ ብዙሃን ዘግበዋል።

በንፋስ ስልክ ላፍቶ ከተማ ብቻ ከአርሶ አደሮቹ የተወሰደ 60 ሄክታር መሬት የአፍሪካ ህብረት አካባቢን ጨምሮ በተለያዩ ቦታዎች ታጥረው እንደሚገኙ የአርሶ አደሮች ኮሚቴው በደብዳቤው አመልክቷል።

በቦሌ፣ በኮልፌ ቀራንዮ፣ በአቃቂ ቃሊቲና፣ በየካ ክፍለ ከተሞች ተመሳሳይ መሬቶች ታጥረው ያለምንም አገልግሎት መቆየታቸውን የሚናገሩት አርሶ አድሮቹ በአማካይ ለ15 አመታት ከፍተኛ ገቢ ማጣታቸውን ለከተማው አስተዳደር አስረድተዋል።

በወቅቱ ለካሬ ሜትር የሚከፈለው የክፍያ መጠን ከአሁኑ ወቅት ጋር ሲነጻጸር ልዩነት እንዳለው ለከንቲባው የገለጹት አርሶ አደሮቹ ይኸው ወቅታዊ ክፍያ ከግምት ውስጥ እንዲገባላቸውም አሳስበዋል።

የከተማዋ አስተዳደር ለአመታት በወሰደው በዚሁ ዕርምጃ ከ134ሺ በላይ አርሶ አደሮች ከይዞታቸው ተፈናቅለው የሚገኙ ሲሆን፣ አስተዳደሩ ወደ 20ሺ አካባቢ የሚጠጉትን በቀጣዮቹ አምስት አመታት መልሶ ለማቋቋም እቅድ መያዙን ሰሞኑን ይፋ ማድረጉ ይታወሳል።

ይሁንና ከቀያቸው የተፈናቀሉ አርሶ አደሮች ቁጥራቸው ከፍተኛ በመሆኑ መልሶ የማቋቋሙ ስራ በርካታ አመታትን ሊፈጅ እንደሚችል ተነግሯል።

የአርሶ አደሮች ኮሚቴ ሰብሳቢ የሆኑት አቶ አሰፋ ረጋሳ የከተማዋ አስተዳደር ወደ ልማት ያልገቡ አካላትን በህጉ መሰረት በመቅጣት ከቦታው ላይ ለተፈናቀሉና በችግር ውስጥ ለሚገኙ አርሶ አደሮች መከፈል ይኖርበታል ሲሉ ለመገናኛ ብዙሃን አስረድተዋል።

በአዲስ አበባ ከተማ ዙሪያ ያሉ የግብርና ቦታዎችን ከአርሶ አደሮች በመረከብ ለባለሃብቶች ለመስጠት ሲካሄድ የቆየው ዘመቻ ወደግጭት ማምራቱና በድርጊቱ በርካታ ሰዎች መሞታቸው ይታወሳል።

ከወራት በፊት በንፋስ ስልክ ላፍቶ እና በቦሌ ክፍለ ከተሞች በተቀሰቀሰ ግጭት በትንሹ ከ15 በላይ ሰዎች መሞታቸው በመገኛኛ ብዙሃን በኩል ሲዘገብ ቆይቷል።

ህገወጥ የተባሉ ግንባታዎችን ጭምር የማፍረሱ ዘመቻ ለጊዜው እንዲቋረጥ ተደርጎ የሚገኝ ሲሆን፣ የከተማው አስተዳደር ከቀያቸው ሊፈናቀሉ ከሚችሉ ተጨማሪ አርሶ አደሮችና ነዋሪዎች ጋር ምክክር እያካሄደ መሆኑን ከሃገር ቤት የተገኘ መረጃ ያመለክታል።