በአዲስ አበባ አትክልት ተራ “ ደረሰኝ የላችሁም” የተባሉ ነጋዴዎች ንብረታቸውን ተወረሰ

ሰኔ ( ሃያ ) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- የከተማው መዘጋጃ በተለምዶ አትክልት ተራ ወደ ሚባለው አካባቢ በመሄድ በአነስተኛ የንግድ ስራ የተሰማሩ አትክልት ነጋዴዎችን ንብረት በመቀማት ከጥቅም ውጭ አድርጓል።

አንዳንድ ነጋዴዎች እንደገለጹት የመዘጋጃ ሰራተኞች “ ደረሰኝ አልሰጣችሁም” በሚል ሽንኩርት፣ ቲማቲምና ሌሎችንም አትክልት በመቀማት እየወሰዱ በመፍጨት ከጥቅም ውጭ አድርገዋቸዋል።

ህጋዊ ፈቃድ ያላቸው ነጋዴዎች ህጋዊ ፈቃድ የሌላቸው ነጋዴዎች አላሰሩን አሉ በማለት ወቀሳ ሲያቀርቡ ቢቆዩም፣ ፈቃድ የሌላቸው ነጋዴዎች በበኩላቸው፣ አትክልት ከህጋዊ ነጋዴዎች ተረክበው እንደሚቸረችሩ በመናገር በድጋሜ ግብር ልንከፍል አይገባም ይላሉ።

ሌሎች ነጋዴዎች ደግሞ በአመቱ መጨረሻ የአነስተኛ ነጋዴዎችን ንብረት መቀማት የተለመደ በመሆኑ አዲስ ነገር አይደለም ሲሉ አስተያየታቸውን የሰጡ ሲሆን፣ የእለት ኑሮአቸውን ለመግፋት ደፋ ቀና የሚሉ ዜጎችን ንብረት ቀምቶ ማውደም ከስነምግባር አንጻር ተቀባይነት እንደሌለው ይገልጻሉ