በአዲስ አበባ ነጋዴዎች በግምት የሚጣልባቸውን ግብር ተቃወሙ

ሰኔ ፳፫ ( ሃያ ሦስት ) ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በወረዳ 11 የሚገኙ ነጋዴዎች ፣ በዘፈቀደ የሚተመነውን የቀን ገቢ ግምት ተንተርሶ የተጣለባቸውን የግብር ከፍያ በመቃወም አቤቱታ ሲያሰሙ፣ በፌደራል ፖሊሶች እንዲበተኑ ተደርጓል። ነጋዴዎች የንግድ ድርጅቶቻቸውን እየዘጉ ፈቃዳቸውን እንደሚመልስ ሲያስጠነቅቁ ውለዋል።
ህዝቡ ወደ ቀበሌ በመሄድ ፈቃዳችንን ተቀበሉን እያለ ቢሆንም፣ ፈቃድም ለመመለስ ከፍተኛ ገንዘብ እንደሚያስከፍል ነጋዴዎች ይናገራሉ ። በመርካቶ አካባቢም በርካታ ሱቆች ተዘግተው መዋላቸውን መረጃዎች ደርሰውናል።
ከሳምንት በፊት ኢሳት የአዲስ አበባ መስተዳድር ምንጮችን ዋቢ በማድረግ ፣ ገዢው ፓርቲ በአዲስ አበባ የግብር ከፋይ ንግድ ማህበረሰብ ተቃውሞ እንዳይነሳበት በተገኘው እድል ሁሉ ቅሬታ ሳያነሱ እንዲረጋጉ ስራዎች ሲሰራ መቆየቱን እንዲሁም አገዛዙ በአንድ በኩል “በተጣለባችሁ የግብር ተመን ላይ ቅሬታ ማቅረብ መብታችሁ ነው” እያለ ፣ በሌላ በኩል ቅሬታ ሰሚ ብሎ የሰየማቸው የየአካባቢው የህዝብ አደረጃጀት የሚባሉት ካድሬዎች መሆናቸው ህዝቡ “ለማን አቤት እንበል” እያለ በማማረር ላይ መሆኑን ዘግቦ ነበር።
የነጋዴው ማህበረሰብ በአንድነት ቆሞ ተቃውሞውን ካላሰማ የግብር ጫናው እየጨመረ እንደሚሄድና መስተዳድሩም ማንኛውንም መንገድ ተጠቅሞ ውሳኔውን እንደሚያስፈጽም የመስተዳድሩ ሰራተኞች ምክራቸውን ለግሰዋል።