በአዲስ አበባ ቤት የማፍረስ እርምጃ ቀጣይ እንደሚሆን ተነገረ

ኢሳት (ግንቦት 26 ፥ 2008)

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለበርካታ ሰዎች ሞት ምክንያት የሆነው አርሶ አደሩንና ሌሎች የልማት ተነሺዎችን የማንሳቱ እቅድ በቂ ካሳና ትክ ቦታን በማቅረብ ቀጣይ እንደሚሆን አርብ አስታወቀ።

ሰሞኑን በከተማዋ ከ10 ለሚበልጡ ሰዎች ሞት ምክንያት የሆነውን ህገወጥ የተባሉ መንደሮችን የማፍረስ እርምጃ ተከትሎ በጉዳዩ ዙሪያ ምክክርን ያካሄደው አስተዳደሩ እቅዱን አስተማማኝና ቀጣይ ለማድረግ ጥናት ማካሄዱን ገልጿል።

በጥናቱ መሰረትም አርሶ አደሩንና ሌሎች የልማት ተነሺዎች መሬታቸውን ለልማት በሚለቁበት ወቅት የተሻለ ካሳ ለማቅረብ የሚያስችልና ምትክ ቦታን ወዲያዉኑ አመቻችቶ ለመስጠት አማራጭ መያዙን ከንቲባው አቶ ድሪባ ኩማ ማስታወቃቸውን ከሃገር ቤት የተገኘ መረጃ አመልክቷል።

ከወራት በፊት አዲስ አበባ ከተማን ወደ ኦሮሚያ ክልል ለማስፋፋት የተያዘው እቅድ ያስከተለውን ተቃውሞ ተከትሎ የከተማ አስተዳደሩ ፕሮግራሙን በመሰረዝ የመልሶ ማልማት ስራውን በአዲስ አበባ ከተማ ብቻ ለመወሰን መግለጹ ይታወሳል።

ከንቲባው ለተነሺዎች በቂ ካሳና ምትክ ቦታ ይሰጣል ቢሉም ምን ያህል አርሶአደሮችና ነዋሪዎች ከይዞታቸው ሊፈናቀሉ እንደሚችሉ የሰጡት ዝርዝር መረጃ የለም።

የከተማዋ አስተዳደር ተወካዮች በቅርቡ በተለያዩ የከተማዋ ስፍራዎች ሊፈርሱ የታሰቡ ቦታዎችን በማስመልከት ከነዋሪዎች ጋር ምክርን ቢያካሄዱም ነዋሪዎች አስተዳደሩ የቤት ቁልፍ ካልተሰጣቸው በስተቀር ከመኖሪያ ቦታቸው እንደማይነሱ አቋም መውሰዳቸው ይታወሳል።

ከሁለት ሳምንት በፊት በከተማዋ ወረዳ 11 የተካሄደው አይነት ተመሳሳይ ዘመቻ በቀጣይ ወረዳ 10 እና 9 ተግባራዊ ይደረጋል ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን በሺዎች የሚቆጠሩ ነዋሪዎች ከቀያቸ ይነሳሉ ተብሎ ተሰግቷል።

በጉዳዩ ዙሪያ ምክክርን ያካሄዱት የከተማዋ አስተዳደር የምክር ቤት አባላት በመንግስት በኩል ያሉ ችግሮች ሊስተካከሉ እንደሚገባም የጠየቁ ሲሆን በሂደቱ የመልካም አስተዳደር ችግሮች መታየታቸውን ገልጿል።

በኦሮሚያ ክልል ከ200 በላይ ለሚሆኑ ሰዎች ሞት ምክንያት በሆነው ተቃውሞ ቅሬታን ሲያቀርቡ የነበሩ ነዋሪዎች ያለበቂ ካሳና ምትክ ቦታ ከቀያቸው እንዲነሱ መደረጉ አግባብ አለመሆኑን ሲገልጹ መቆየታቸው ይታወቃል።

የከተማዋ አስተዳደር የነደፈው አዲስ እቅድም በርካታ አርሶ አደሮች ከአዲስ አበባ ዙሪያ ሊያፈናቅል ይችላል ሲሉ ስጋታቸውንሲገልጹ ቆይተዋል።