ጥር ፬ (አራት)ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በአዲስ አበባ ፉሪ አካባቢ መኖሪያ ቤታቸው በላያቸው ላይ የፈረሰባቸው የአካባቢው ነዋሪዎች እና ብቻውን የቀረው የፉሪ ደብረገነት ኡራኤል ቤተክርስቲያን ሕልውና አደጋ ላይ መሆኑን ምንጮቻን ተናግረዋል። በአካባቢው ነዋሪ የነበሩ 7 ሽህ 500 አባውራዎች በአጠቃላይ በድምሩ ከ30 ሽህ በላይ የሚገመቱ ዜጎች ከመኖሪያ ቀያቸው ተፈናቅለዋል። የተገደሉም መኖራቸውን አባቶች ይናገራሉ።
ተፈናቃይ ነዋሪዎች በአፍራሽ ግብረሃይሉ በአስገዳጅ ሃይል ከ አካባቢው እንዲርቁ ተደርገዋል። የተወሰኑት ደግሞ አሁንም በቤተክርስቲያኗ ጥጋት ስር ተከልለው ይኖራሉ። መኖሪያ ቤታቸው በላያቸው ላይ መፍረሱን በመቃወማቸው የታሰሩ እና ቤተሰባቸውን በትነው ከአካባቢው በመራቅ በወዳጅ ዘመድ ቤት የተጠለሉ ሲኖሩ ቁጥራቸው በውል የማይታወቁ ደግሞ በታጣቂዎች በግፍ መገደላቸውን እማኞች ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል።
ለዘመናት ጎጆ ቀልሰው ይኖሩ የነበሩ ዜጎችን በክረምት በላያቸው ላይ መኖሪያቸውን በማፍረስ ቦታውን ለጋራ መኖሪያ ቤቶች ኮንዶሚኒየም እና ለቄራ አገልግሎት ግንባታ ለመስጠት ስፍራው ታጥሯል።
የፉሪ ደብረገነት ኡራኤል ቤተክርስቲያን የአካባቢው ነዋሪዎች መፈናቀላቸውን ተከትሎ የአዲስ አበባ አገረ ስብከት ለቤ/ክ ካህናት የሶስት ወራት ደመወዝ ክፍያ ፈፅሟል። ቤተክርስቲያኗም ባላት አቅም ለሶስት ወራት ተፈናቃዮችን ስትረዳ ቆይታለች። በአሁኑ ወቅት ግን ብቻውን የቀረው ቤተክርስቲያን ካህናት ተበትነው ቤተክርስቲያኗ ልትዘጋ ትችላለች ሲሉ ስጋት ያደረባቸው ሲሆን የሟቾች ስም እየተጠራ የሚዘከርባት ቤተ ክርስቲያን እንድትሆን ምእመናኑ እገዛ ያደርግላቸው ዘንድ የተማጽኖ ጥሪ አቅርበዋል።
በመልሶ ማልማት ስም በአዲስ አበባ ዙሪያ የሚገኙ መኖሪያ ቤቶችን በማፍረስ ላፍቶ ክፍለ ከተማ፣ ሀና ማርያም፣ ፉሪ አካባቢ ተደጋጋሚ ሕዝባዊ ተቃውሞዎች ተደርገው የብዙ ንጹሃን ዜጎች ሕይወት ማለፉን ኢሳት በተደጋጋሚ ጊዜያት ሲዘግብ መቆየቱ ይታወሳል።