ኀዳር ፱(ዘጠኝ) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-የማጅራት ገትር ወረርሺኝ ጋር ተያይዞ ከሳምንት በፊት ለ10 ተከታታይ ቀናት ዕድሜያቸው ከ1 እስከ 29 ኣመት ክልል ላሉ ዜጎች ክትባት የመስጠት ሒደት የተከናወነ ቢሆንም አፈጻጸሙ ከተጠበቀው ውጪ ሆኖአል፡፡ በተለይ ዕድሜያቸው ከ29 ዓመት በላይ መከተብ አያስፈልጋቸውም፣ ከተከተቡ የጎንዮሽ ችግር ያመጣባቸዋል መባሉ ግማሽ ያህል የህብረተሰብ ክፍል ቢሞትም ግድ የለንም እንደማለት ተደርጎ በመቆጠሩ የጤና ጣቢያዎች በክትባት ፈላጊዎች ተጨናንቀው ታይተዋል፡፡ ዕድሜያቸው ከ29 ዓመት በላይ የሆኑና ጎልማሶች ጭምር ለክትባት ተሰልፈው ታይተዋል፡፡ በዚህም ምክንያት የክትባት አቅርቦትና የፍላጎት አለመጣጣም መከሰቱ ታውቆአል፡፡
ወርረሽኙ በተለይ በአዲስአበባ አገርሽቶ ከቁጥጥር ውጪ እንዳይወጣ ሥጋት መኖሩ ታውቆአል፡፡ ወርረሽኙን ለመከላከል ዋንኛው ዘዴ ክትባት ሲሆን አንዴ ክትባት የወሰዱ ሰዎች ዕድሜ ልክ ከበሽታው ሥጋት ነጻ መሆን እንደሚሆኑ ያገኘነው መረጃ ይጠቁማል፡፡