(ኢሳት ዜና –ሐምሌ 18/2009)የአዲስ አበባ ነዋሪዎች አንዴ በግብር፣ሌላ ጊዜ በመፈናቀል ሲብስ ደግሞ በኑሮ ውድነት በአገዛዙ መከራቸውን እያዩ መሆናቸውን ይናገራሉ።
አበሳና መከራው ግፍና በደሉ የበዛባቸው የከተማዋ ነዋሪዎች እሮሮአቸውን ለሮይተርስ ገልጸዋል።ሮይተርስ ያነጋገራቸው የከተማዋ ነዋሪዎች በ360 ሔክታር ላይ የሚኖሩና 3 ሺ የሚደርሱ ቤቶቻቸው ከሚፈርስባቸው መካከል ያሉትን ነበር።
እናም ነዋሪዎቹ ከኖርንበት አካባቢና ቀየ ሀብት ንብረታችንን ጥለን እንድንሄድ ተገደናል ነው ያሉት።
አቡበከር በፈራረሰ የንግድ ማእከሉ አጠገብ ሆኖ ለሮይተርስ እንደገለጸው አባቱ ለፍተውና ደክመው ለ40 አመታት የሰሩበትን የንግድ ተቋም በአንድ ጀንበር አጥቷል።
እንደ አቡበከር ገለጻ ከአባታቸው የወረሱት የንግድ ማእከል ካፌ፣ሆቴልና የቅርሳቅርስ ሱቆች ነበሩት።
እናም ምንም ባላወቁበትና ቅድሚያ ማስጠንቀቂያ ሳይሰጣቸው በአንድ ጀምበር ፍርስርሱ እንደወጣባቸው አቡበከር ተናግሯል።
ጸጋዬ የተባለው ወጣት ደግሞ በአፍሪካ ህብረት ህንጻ አቅራቢያ ክረምቱ እስኪያልፍ እንጠብቃችኋለን ካሉ በኋላ ድንገተኛ ነገር ገጥሞናል በሚል በ3 ቀናት ብቻ ቤታቸው መፍረሱን ነው የተናገረው።
በህጉ መሰረት የአዲስ አበባ አስተዳደር ቤት ሲያፈርስና ሰዎችን ሲያፈናቅል ምትክ ቦታ የመስጠትና የጉዳት ካሳ መክፈል ይጠበቅበታል።
ይህ መሆኑ ቀርቶ ያለምንም ማስጠንቀቂያ ቤታቸው መፍረሱ ነዋሪዎችን አስመርሯል።
በአዲስ አበባ የመሬት ዋጋ እጅግ በመናሩና ከፍተኛ የሀብት ምንጭ በመሆኑ መንግስትና ባለሃብቶች እንዲሁም ባለስልጣናት እየተሻረኩ ነዋሪዎችን በማፈናቀል እየተቀራመቱት መሆኑን ሮይተርስ ያነጋገራቸው ጉዳተኞች ገልጸዋል።
በዚህም ምክንያት ሶስት ሺ ቤቶች በሚቀጥለው ሶስት አመት ውስጥ ይፈርሳሉ ነው የተባለው።
የአዲስ አበባ የመሬት ሊዝ ዋጋ በአፍሪካ ካሉት ሀገራት ከፍተኛው መሆኑን መረጃዎች ያመለክታሉ።አንድ ስኩዬር ሜትር በ15 ሺ ብር ዋጋ ይቸበቸባል።
ለነዋሪዎቹ ካሳ ሲከፈል ግን በመሬቱ ላይ በሌለው ግድግዳና ጣራ ብቻ ስለሆነ ባለይዞታ ነዋሪዎች እራቁታቸውን እንደሚቀሩ ሮይተርስ ዘግቧል።
በአዲስ አበባ ከቤተመንግስት እስከ አፍሪካ ህብረት ያለው ሶስት መቶ ሄክታር ቦታ በዚህ አመት ብቻ እንደሚፈርስ ኢሳት መዘገቡ ይታወሳል።