በአዲስ አበባ በተለምዶ ቆሼ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ የተከሰተው አደጋ በአካባቢው በመገንባት ላይ ባለ በባዮ-ጋዝ ፕሮጄክት ምክንያት መሆኑ ተገለጸ 

ኢሳት (መጋቢት 4 ፥ 2009)

በአዲስ አበባ በተለምዶ ቆሼ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ለ65 ሰዎች ሞት ምክንያት የሆነው አደጋ በአካባቢው በመገንባት ላይ ያለ የባዮጋዝ ፕሮጄክት ምክንያት መሆኑን ነዋሪዎች ገለጹ።

በከተማዋ አስተዳደር በመካሄድ ላይ ላለው ለዚሁ ግንባታ መሬቱን ለማስተካከል ሲከናወኑ የቆዩ ስራዎች በቆሻሻ ክምሩ ላይ ጭነት ማሳደሩንና ለአደጋው መንስዔ መሆኑን ሮይተርስ ነዋሪዎችን ዋቢ በማድረግ ሰኞ ዘግቧል። አቶ ብርሃኑ ደግፌ የተባሉ የአካባቢው ነዋሪና መጠለያቸው ከአደጋው የተረፉ እማኝ በስፍራው ሲካሄድ የነበረው የባዮ ጋዝ ፕሮጄክት ዝግጅት ለቆሻሻ ክምሩ መናድ መስዔ ሆኗል ሲል ለዜና አውታሩ ገልጸዋል።

አቶ ኢብራሂም መሃመድ የተባሉ ሌላ የአካባቢው ነዋሪ ለባዮ ጋዝ ግንባታ ሲካሄድ የቆየው ዝግጅት በቆሻሻ ክምሩ ላይ ከፍተኛ ግፊት በማሳድር አደጋው ሊደርስ መቻሉን አስረድተዋል። በዚሁ ስፍራ በትንሹ 50 መኖሪያ ቤቶች ይገኙ እንደነበር የሚናገሩት ዕማኞች በእያንዳንዱ መኖሪያ ቤት ሰባት ሰዎች ይኖሩ እንደነበር ተናግረዋል።

የአዣንስ ፍራንስ ፕሬስ እና የሮይተርስ ጋዜጠኞች የቆሻሻ ክምሩ ክፍተት የሚታይበት መሆኑን እንደታዘቡ ገልጸው ተጨማሪ የቆሻሻ ክምችት ሊናድ እንደሚችል ባቀረቡት ሪፖርት አስፍረዋል።

በተለምዶ ቆሼ ተብሎ የሚጠራው አካባቢ ባለፉት 40 አመታት ከመዲናይቱ አዲስ አበባ የሚወጡ የተለያዩ ቆሻሻዎችን ለማጠራቀም ሲያገለግል እንደነበር ይነገራል።

አደጋው ቅዳሜ ምሽት በደረሰ ጊዜ የሟቾች ቁጥር 46 እንደነበር ቢነገርም ሰኞ የሟቾቹ ቁጥር ወደ 50 ማደጉ ተገልጿል።

ይሁንና በርካታ የገቡበት ያልታወቀ ነዋሪዎች በመኖራቸው ምክንያት የሟቾች ቁጥር ሊጨምር ይችላል ተብሎ የተሰጋ ሲሆን፣ የነብስ አድን ሰራተኞች ለመገኛኛ ብዙሃን አስረድተዋል።

የከተማ አስተዳደር ቃል አቀባይ የሆኑት አቶ አማረ መኮንን 49 መኖሪያ ቤቶች በአደጋው እንደወደሙ አረጋግጠዋል።

በአሳዛኙ አደጋ ህይወታቸውን ካጡት ሰዎች መካከል የ19ኙ የቀብር ስነ-ስርዓት ሰኞ ከሰዓት በኋላ በለቡ ገብርዔል አካባቢና በቆልፌ ቀራንዮ በሚገኘው መካነ መቃብር ተፈጽሟል። ከሟቾች መካከል በትንሹ 15 የሚሆኑት ህጻናት መሆናቸው ታውቋል።

በአሁኑ ወቅት ወደ 28 የሚጠጉ ሰዎች በሆስፒታል የህክምና አገልግሎት እያገኙ እንደሆነ የተናገሩ የከተማዋ አስተዳደር ባለስልጣናት ወደ 300 አካባቢ የሚጠጉ የአካባቢው ነዋሪዎች በጊዜያዊ መጠለያ እንዲያርፉ መደረጉን ባለስልጣናት ገልጸዋል።

በተለምዶ ቆሼ ሰፈር ተብሎ በሚጠራው አካባቢ በመጠራቀም ላይ ካለው የቆሻሻ ክምችት 50 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ሃይል ለማመንጨት ከሶስት አመት በፊት 120 ሚሊዮን ዶላር ፕሮጄክት መጀመሩ ይታወሳል።

ከዚሁ ፕሮጄክት በመካሄድ ላይ ያለው የመሬት መደልደልና ሌሎች ተያያዥ ስራዎች በቆሻሻ ክምሩ ላይ ግፊት ማሳደሩንና ለቅዳሜ አደጋ ምሽቱ ምክንያት መሆኑን ሮይተርስና አዣንስ ፍራንስ ፕሬስ ነዋሪዎች ዋቢ በማድረግ ባቀረቡት ዘገባ አስፍረዋል።