በአዲስ አበባ መኖሪያ ቤታቸው ለአረንጓዴ ልማት ይፈለጋል ሰዎች ተቃውሞ አሰሙ

ኢሳት (ግንቦት 12 ፥ 2008)

በአዲስ አበባ ከተማ ሃና ማሪያም ተብሎ በሚጠራ አካባቢ የሚኖሩ ወደ 3ሺ አካባቢ ነዋሪዎች አካባቢው በአረንጓዴ ልማት የሚሆን ነው ተብሎ ሊነሱ መሆናቸውን ተቃወሙ።

ከከተማው አስተዳደር ተወካዮች ጋር በቅርቡ ምክክርን ያደረጉት እነዚሁ ነዋሪዎች፣ መንግስት የቤት ቁልፍን ካስረከባቸው የመኖሪያ ቀያቸውን እንደማይለቁም ለባለስልጣናቱ አስረድተዋል።

በዚሁ ውይይት ላይ የተሳተፉና የተቀረጸ መረጃ ለኢሳት ያደረሱ ነዋሪዎች  በገዢው መንግስት ኢህአዴግና በከተማዋ ነዋሪዎች መካከል መተማመን እየጠፋ መምጣቱንም ለተወካዮች ሲገልጹ ተደምጠዋል።

ነዋሪዎቹ ሰፍረው ከሚገኙበት አቅራቢያ ሌላ አማራጭ እያለ ወደ 3ሺ የሚጠጉ ነዋሪዎችን ከቀያቸው ለማንሳት የሚደረገው ጥረት የህብረተሰቡን ችግር ግምት ውስጥ ያካተተ እንዳልሆነም ነዋሪዎቹ ገልጸዋል።

መሰረተ ልማቶቹ ባልተሟሉበት ስፍራ በችግር ውስጥ እንደሚኖሩ የሚናገሩት ነዋሪዎች ቦታዎች ለልማት ይፈለጋሉ እየተባለ ሰዎችን ያለአማራጭ ማፈናቀሉ ተገቢ አለመሆኑንም ለመንግስት ተወካዮች አስረድተዋል።

በነዋሪዎችን በመንግስት በኩል መተማመን የለም ሲሉ የገለጹት አስተያየት ሰጪዎቹ የከተማዋ አስተዳደር ቤቶችን ገንብቶ ቁልፉን እስካልሰጣቸው በስተቀር በሚገባ ቃል ብቻ የመኖሪያ ቀያቸውን እንደማይለቁም አቋማቸውን በጋራ ገልጸዋል።

የከተማዋ አስተዳደር በቅርቡ ከ1977 እስከ 2003 ዓም ድረስ በህገወጥ መንገድ ተገንብተዋል የተባሉ መኖሪያ ቤቶችን ካርታ እንደሚሰጥ ቃልን ቢገባም የመኖሪያ ስፍራዎቹ በስጋት ውስጥ መሆናቸውን ነዋሪዎች አክለው አስታውቀዋል።

ባለፈው አመት የተካሄደው ብሄራዊ ምርጫ ምክንያት በማድረግ የከተማው አስተዳደር ከበርካታ ህገወጥ መኖሪያ ቤቶች ካርታን እንደሚሰት ቃል መግባቱ ይታወሳል።

ይሁንና  መንግስት የገባውን ቃል በማጠፍ በርካታ ነዋሪዎች ከቀያቸው እያፈናቀለ እንደሚገኝ የመኖሪያ ቤታቸው በመፍረስ ላይ የሚገኘው የወረገኑ ነዋሪዎች በመግለጽ ላይ ናቸው።

የከተማዋ አስተዳደር በበኩሉ እንዲፈርሱ የተደረጉት ቤቶች ህገወጥ የነበሩ ናቸው ሲል አስተባብሏል።