በአዲስ አበባ በምግብ እጥረት ምክንያት ትምህርት የሚያቋርጡ እና ውጤታማ መሆን ያልቻሉ ልጆች ቁጥር እያሻቀበ ነው። የትምህርት ቤቶችን ቁጥር በመጨመር ሕፃናት በነፃ ትምህርት የሚያገኙበት እድል ቢመቻችም፣ በቂ ምግብ አለማግኘታቸው ተከትሎ ብዙዎችን ከትምህርት ገበታቸው እያፈናቀላቸው መሆኑ የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ አስታውቋል።
ባለፈው ዓመት ከበጎ አድራጊ መንግስታዊ ካልሆኑ ግብረሰናይ ድርጅቶች በትምህርት ቤት ምግብ ይቀርብላቸው የነበሩት ሕጻናት፣ አምስት ሺህ ነበሩ። በምግብ እጦትና ቤተሰብ ገቢ በማጣቱ ምክንያት ትምህርታቸው ለማቋረጥ የተገደዱ ታዳጊ ሕጻናት ካለፈው ዓመትጋር ሲነጻፀር በእጥፍ መጨመሩን ትምህርት ቢሮው በአዲሱ ጥናቱ አመላክቷል።
በያዝነው ዓመት በተደረገው ጥናት የተረጂዎቹ ታዳጊ ሕጻናት ቁጥሩ እጅግ በመጨመሩ በእናት በጐ አድራጐት ማህበር በኩል ብቻ ከሃያ ሽህ በላይ ተማሪዎች ምግብ እየቀረበላቸው ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ ተደርጓል። በተጨማሪ በበጐ አድራጊ ግለሰቦችና ሌሎች ድርጅቶች ተጨማሪ 10 ሺህ ህፃናት የምሣ ምገባ ተጠቃሚ መሆናቸውን ትምህርት ቢሮው ማስታወቁን ሸገር ኤፍኤም ዘግቧል።