በአዲስአበባ ክፍለከተሞች በደንብ አስከባሪ ስም በርካታ ቁጥር ያላቸውን በህዝቡ ውስጥ የጸጥታ ክትትልና ቁጥጥር ሥራ የሚያከናውኑ ወጣቶችን መመልመል ተጀመረ፡፡

ጥር ፲፪ ( አሥራ ሁለት )ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- ለስራ መደቡ በመስፈርትነት የተቀመጠው ዕድሜ ከ18 ዓመት ያላነሰ ከ30 ዓመት ያልበለጠ ሆኖ የስነምግባር ችግር እንደሌለበት ከሚኖርበት ወረዳ ማስረጃ ማቅረብ የሚችል ወይንም ቀድሞ ከሚሰራበት ድርጅት በስነምግባር ችግር ያልተቀነሰ፣ የከተማዋን ነዋሪዎች በእኩልነት ማገልገል የሚችል እንዲሁም በቀድሞ የሁለተኛ ደረጃ ያጠናቀቁ ወይንም በአዲሱ ካሪኩለም 10ኛ ክፍል ያጠናቀቁ የሚል ይገኝበታል።
ምልመላውን ለማከናወን በየወረዳው ኮሚቴ እንደሚቋቋምና አመልካቾች መሰረታዊ የውትድርና ስልጠና ወደሚያገኙበት ተቋም ከመላካቸው በፊት ግልጽ በሆነ ቦታ ስም ዝርዝራቸው ተለጥፎ በሕዝቡ አስተያየት ይሰጥባቸዋል ተብሏል፡፡
ምልምሎቹ ከስልጠና በሃላ በወረዳ ደንብ ማስከበር ጽ/ቤት በፈረቃ አስተባባሪና እና በቁጥጥር ኦፊሰርነት ሙያ ይመደባሉ ተብሏል፡፡
በአዲስአበባ በደንብ ማስከበር አገልግሎት ከሕገወጥ ግንባታ ቁጥጥር ጋር በእጅጉ የተቆራኘ ቢሆንም ባለሙያዎቹ በግዴታ ጭምር በጸጥታ ማስከበር ስም የስለላ ስራዎችን እንዲያከናውኑ እንደሚገደዱ ዘጋቢያችን ምንጮቹን ዋቢ በማድረግ ዘግቧል።
በአሁኑ ሰዓት ምልመላው ያለቀነገድብ በመካሄድ ላይ ሲሆን እስካሁን ባለው መረጃ በየክፍለከተሞቹ ወጣቶች ለመመዝገብ ፍላጎት እያሳዩ አይደለም፡፡