በአዲስአበባ ከሚገኙ 58 የአሸከርካሪ ማሰልጠኛ ተቋማት ብቃት ያላቸው 10 ብቻ ናቸው

መስከረም ፳፪(ሃያ ሁለት)ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመንገድና ትራንስፖርት ቢሮ ቢሮው በአዲስ አበባ ከተማ በሚገኙ የአሸከርካሪዎች ማሰልጠኛ ተቋማት ላይ ያደረገውን ግምገማ ውጤት ተከትሎ ማንኛውም የመንጃ ፈቃድ ሰልጣኝ ከጥቅምት1 ቀን 2006 በፊት በማናቸውም የአሸከርካሪዎች ማሰልጠኛ ተቋማት ውስጥ ትምህርት እንዳይጀምሩ አስጠነቀቀ፡፡ ዛሬ ይፋ በተረደገው የጥናት ውጤት መሰረት ከ58 የማሰልጠኛ ተቋማት ዝቅተኛውን መስፈርት ማሟላት የቻሉት 10 ያህሉ ብቻ ናቸው ብሎአል።

በአዲስ አበባ ከተማ ካሉ 58 የአሽከርካሪ ማሰልጠኛ ተቋማት ውስጥ 48 ያህሉ የተቀመጠውን መስፈርት ባለማሟላታቸው ለጊዜው ማሰልጠን እንዲያቆሙ መወሰኑን በዛሬው ዕለት ቢሮው የስራ ኃላፊዎች በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ አስታውቀዋል፡፡ እርምጃው ከግዜ ወደግዜ በአስደንጋጭ ፍጥነት እያደገ የመጣውን የትራፊክ አደጋ ለመቀነስ ከሚወሰዱ እርምጃዎች አንዱ ነው ተብሎአል፡፡

የአዲስ አበባ መንገድና ትራንስፖርት ቢሮና የፌዴራል ትራንስፖርት ባለስልጣን ባወጣው 13 መስፈርቶች መሰረት 58 የማሰልጠኛ ተቋማት እንዲመዘኑ ተደርጓል።በዚሁ መሰረት 85 በመቶ ያመጡ የአሽከርካሪ ማሰልጠኛ ተቋማት የጽሁፍ ማስጠንቀቂያ ደርሶአቸው ማስልጠናቸውን እንዲቀጥሉ ሲፈቀድ ፥ ከዚያ በታች የሆኑት ግን ያለምንም ቅድመ ሁኔታ የማሰልጠን ፈቃዳቸው እንደሚሰረዝ ታውቋል።

ሆኖም በ2004 ዓ.ም በአዲስ አበባ ባሉ 58 የአሽከርካሪ ማሰልጠኛ ተቋማት ላይ በተደረገ ግምገማ 58 ያህሉ ከሰማንያ በመቶ በታች በማምጣታቸው ፤ በአዲስ አበባ የማለፊያ ነጥቡ ዝቅ እንዲል ተወስኗል። ይህም ሆኖ ከ70እስከ 80 በመቶ ያመጡ በጽሁፍ ማስጠንቀቂያ ማሰልጠን እንዲቀጥሉና በሁለት ወራት ውስጥ ክፍተታቸውን እንዲያስተካክሉ ፣ ከ60 እስከ69 ነጥብ 9 በመቶ ያመጡ ደግሞ ማሰልጠን አቁመው ጉድለታቸውን እንዲያሟሉ ፣ ከ59 ነጥብ 9 በመቶ በታች ያመጡ ደግሞ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ፍቃዳቸው እንዲሰረዝ መወሰኑን የስራ ኃላፊዎቹ በዛሬው መግለጫቸው አስታውቀዋል፡፡

ከአሸከርካሪ የማሰልጠኛ ተቋማት ባለቤቶች መካከል አንዱ ስለጉዳዩ አስተያየት ተጠይቀው ጥናት የተባለው ውጤቱ እንዳልደረሳቸው በመጥቀስ ዝርዝር አስተያየት ለመስጠት እንደሚቸገሩ፤ ግን የጥናቱ ሒደት ግልጽነት የጎደለው በመሆኑ ጥሩ ውጤት እንደማይጠብቁ ተናግረዋል፡፡ በተለይ ከመንጃ ፈቃድ አሰጣጥ ጋር ትልቅ ችግር ያለው በራሱ በፌዴራል የትራንስፖርት ባለስልጣንና በአ/አ መንገድና ትራንስፖርት ቢሮ ሆኖ ሳለ ራሱ አጥፊዎቹ፣ እንደገና ማሊያ ቀይረው አጥኚና ፈራጅ መሆናቸው ያሳዝናል ብለዋል