ታኀሳስ ፩(አንድ) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ዘጋቢያችን በአራት ኪሎ፣ በቦሌ፣ በካዛንቺስ፣ በልደታ አካባቢዎች የሚገኙ ነዳጅ ማደያዎችን ተዘዋውሮ እንደተመለከተው በብዙዎቹ ማደያዎች በዛሬው እለት ነዳጅ ቢኖርም ነዳጅ ለመቅዳት የተሰለፉ ተሸከርካሪዎች በመብዛታቸው ረጃጅም ሰልፎች መታጣቸውንና የትራፊክ መጨናነቅ መከሰቱን መታዘብ ችሎአል፡፡ በዓለም ገበያ ላይ የነዳጅ ዋጋ መቀነስን ተከትሎ ከትላንትና ህዳር 30 ቀን 2007 ዓ.ም ጀምሮ ንግድ ሚኒስቴር መጠነኛ ቅናሽ አድርጓል።
ሚኒስቴሩ በነዳጅ ምርቶች ላይ በየወሩ መጨረሻ ክለሳ የሚያደርግ ሲሆን እስከዛሬ በነበረው የተለመደ አሰራር ወይ ይጨምራል፤ ወይንም ባለበት እንዲቀጥል ሲያደርግ ቆይቷል፡፡ በአለም ገበያ ላይ በከፍተኛ መጠን ያለውን ቅናሽ መሰረት በማድረግ ባለፉት 15 ቀናት ጊዜ ውስጥ የነዳጅ የችርቻሮ ዋጋ ሲቀንስ ይህ ለሁለተኛ ጊዜ ነው፡፡
ሆኖም ማደያዎቹ የዋጋ ቅናሽ ሲደረግ በስቶክ ውስጥ ያለ ምርታቸው ቀደም ባለ ዋጋ የገዙት በመሆኑ እንደማያዋጣቸው በመግለጽ ላለመሸጥ አንገራግረው የነበረ ቢሆንም ንግድ ሚኒስቴር ባደረገው ጫና በሙሉ ወደስራ ሊመለሱ ችለዋል፡፡ ካለፉት ስድስት ወራት በፊት የነዳጅ ዋጋ በበርሜል 115 የአሜሪካ ዶላር የነበረ ሲሆን በአሁኑ ወቅት ወደ 67 የአሜሪካ ዶላር ያሽቆለቆለ መሆኑ ይታወቃል፡፡