በአዲሱ ጠ/ሚኒስትር አብይ አህመድ ከግድያ ሙከራ ጀምሮ የተለያዩ ሴራዎችን ሲያሴሩ የነበሩ ሰዎች በቁጥጥር ስር እየዋሉ ነው
(ኢሳት ዜና ሰኔ 27 ቀን 2010 ዓ/ም) በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የሚካሄዱ ግጭቶችን በማስተባበር እንዲሁም በአዲስ አበባ ውስጥ በዶ/ር አብይ አህመድና ሌሎችም የኢህአዴግ ባለስልጣናት ላይ የግድያ ሙከራ ለማድረግ ሲያቀናብሩ ከነበሩት ሰዎች መካከል የተወሰኑት መያዝ መጀመራቸውን ምንጮች ገልጸዋል። በአሁኑ ሰዓት መቀሌ ከሚገኘው ከቀድሞው የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ሜ/ጄ ተክለ ብርሃን ወልዳረጋይ ጋር በመሆን የተለያዩ እርምጃዎችን ለመውሰድ እቅዶችን ሲነድፉ ከነበሩት ሰዎች መካከል የኢንሳ ምክትል ዳይሬክተር የነበረውና በሁዋላ በትምህርት ሚኒስቴር ውስጥ የተመደበው ቢኒያም ተወልደ ትናንት በቁጥጥር ስር ውሎአል። የግለሰቡ መኖሪያ ቤት ዛሬ የተበረበረበ ሲሆን፣ የተለያዩ ሰነዶችና ላፕቶፖች ተወስደዋል። የኢሳት ምንጮች እንደገለጹት የእነ ጄ/ል ተክለብርሃን ቡድን ከቀድሞው የሜቴክ ሃላፊ ጄ/ል ክንፈ ዳኘው እና ከአንዳንድ የህወሃትና የብአዴን ሰዎች ጋር በመሆን በአማራ ክልል ከሱዳን ጋር በሚያዋስኑ ቦታዎች፣ በአማራ እና በኦሮምያ ክልል አዋሳኝ ቦታዎች፣ በቤንሻነጉል ጉሙዝ፣ በአፋር እንዲሁም በሶማሊ አካባቢዎች የተለያዩ ግጭቶችን በማስነሳት ደም እንዲፈስ ሲያስደርጉ ቆይተዋል።
ምንጮች እንደገለጹት የኢንሳ የቀድሞ ባለስልጣናትና የቀድሞው የሜቴክ ሃላፊው የዶ/ር አብይን መንግስት ለመጣል ከመደቡት በብዙ ሚሊዮኖች የሚቆጠር ገንዘብ በተጨማሪ፣ ከሶማሊ ክልል መሪ አቶ አብዲ ሙሃመድ ዳጎስ ያለ ገንዘብ ተሰጥቷቸዋል።