(ኢሳት ዜና–ሕዳር 28/2010)
አለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም አይ ኤም ኤፍ በማኔጂንግ ዳይሬክተሩ የሚመራ የልዑካን ቡድንን ወደ ኢትዮጵያ ለመላክ መዘጋጀቱ ታወቀ።
ተቋሙ ቡድኑን ወደ ኢትዮጵያ የሚልከው በሀገሪቱ የተከሰተው ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ እጥረትና የኢኮኖሚው ሁኔታ እያሳሰበው በመምጣቱ መሆኑ ታውቋል።
የሀገሪቱ ተጠባባቂ የውጭ ምንዛሪ ወደ 700 ሚሊየን ዶላር የወረደ ሲሆን በውጭ ምንዛሪ ዕጥረት በጅቡቲ የተከማቹ እቃዎችን ማንሳት እንዳልተቻለም የኢሳት ምንጮች ገልጸዋል።
በወጭ ንግድ የተሰማሩም እስከ አንድ አመት ለውጭ ምንዛሪ ወረፋ እንደሚጠብቁም ታውቋል።
በኢትዮጵያ የተከሰተው የውጭ ምንዛሪ እጥረትበሀገሪቱ ኢኮኖሚያዊ እንቅስቅሴ ላይ ብርቱ ማነቆ ሆኖ ተገኝቷል።
በዚህም በአመቱ ሊጀመሩ የታቀዱ በርካታ ፕሮጀክቶች መደርደሪያ ላይ የቀሩ መሆናቸውም ታውቋል።
ከጅቡቲ ወደብ ወደ ኢትዮጵያ ሊሰራ የታቀደው የ550 ኪሎ ሜትር የነዳጅ ማስተላለፊያ መስመር በዚህ አመት ሊጀመር መርሃ ግብር ከተያዘለት በኋላ በውጭ ምንዛሪ እጥረት ምክንያት ተሰርዟል።
የሐገሪቱ ተጠባባቂ የውጭ ምንዛሪ በጣም ዝቅተኛ እንደሆነ የሚገልጹት የኢሳት ምንጮች ለ3 ሳምንታት ብቻ የሚበቃ ሲሆን መጠኑም 700 ሚሊየን ዶላር እንደሆነም ተመልክቷል።
በዚህ የውጭ ምንዛሪ እጥረት ኢትዮ-ቴሌኮምና የኢትዮጵያ ንግድ መርከብ ድርጅት ያለባቸውን ዕዳ ለመክፈል የውጭ ምንዛሪ እጥረት ችግር እንደገጠማቸው በይፋ አስታውቀዋል።
የኢትዮጵያ ንግድ መርከብ በብሔራዊ ባንክ ያስቀመጠው የራሱ 100 ሚሊየን የአሜሪካን ዶላር በተከሰተው እጥረት ሳቢያ ሊለቀቅለ እንዳልቻለም ይፋ ሆኗል።
የውጭ ምንዛሪ እጥረቱ በነዳጅና በመድሃኒት ግዢ ላይ ጭምር ተጽእኖ ባመጣበት በአሁኑ ወቅት በወጭ ንግድ የተሰማሩ ነጋዴዎችም የውጭ ምንዛሪ ለማግኘት ከፍተኛ ችግር ገጥሟቸዋል።
የውጭ ምንዛሪው ለነጋዴዎቹ እየተሰጠ ያለው በወረፋ ሲሆን የተሳካላቸው በ8 ወራት ውስጥ ሲያገኙ ያልተሳካላቸው እስከ አንድ አመት መጠበቅ እንደሚገደዱ የብሔራዊ ባንክ ምንጮች ለኢሳት ገልጸዋል።
በዚሁ የውጭ ምንዛሪ እጥረት ጅቡቲ ወደብ የደረሱ 2ሺ ያህል ኮንቴነሮች በወደብ ኪራይ ሂሳብ ተይዘዋል።
የሀገሪቱ የውጭ ምንዛሪ እጥረት በከፍተኛ ደረጃ በተባባሰበት በአሁኑ ወቅት የሀገሪቱ አመታዊ እዳ ክፍያ ከነወለዱ 2 ቢሊየን ዶላር መድረሱንም ለኢሳት የደረሰው መረጃ አመልክቷል።
ከዚህ ክፍያ ውስጥ አብዛኛው ለቻይናው ኢምፖርት ኤክስፖርት ኤግዚም ባንክ የሚከፈል መሆኑም ታውቋል።
ቀውሱ በተባባሰበት በአሁኑ ወቅት የአለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም አይ ኤም ኤፍ ማኔጂንግ ዳይሬክተር ክሪስቲን ላጋርድ ወደ ኢትዮጵያ የሚያደርጉት ጉዞ በሚስጥር እንዲያዝ በብሔራዊ ባንክ ገዢ ተክለወልድ አጥናፉ መጠየቁ ታውቋል።
ነገር ግን ጥያቄውን አይ ኤም ኤፍ ስላልተቀበለው የላጋርድ ጉዞ ይፋዊ እንደሚሆንም ለማወቅ ተችሏል።
በጊዜው በይፋ የተቆረጠው ቀን ባይታወቅም በቅርቡ አዲስ አበባ የሚገቡት ዳይሬክተሯ ለሀገሪቱ በሚሰጡ ብድሮች ላይ እንደሚመክሩ ይጠበቃል።
ሆኖም አለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም ብድሩን ከመልቀቁ በፊት የግዙፍ ፕሮጀክቶች ስራ እንዲቋረጥ እንዲሁም ቴሌኮሚኒኬሽንን የመሳሰሉ ግዙፍ መንግስታዊ ተቋማትን ወደ ግል ማዛወር በቅድመ ሁኔታነት ሊቀመጥ ይችላል ሲሉ የኢኮኖሚ ባለሙያዎች ይገልጻሉ።
ይህ በእንዲህ እንዳለም በባህረሰላጤው ሀገራት ከተፈጠረው ቀውስ ጋር በተያያዘ በአረቡ አለም ውዝግብና መገለል ከገጠማት ኳታር ጋር የኢትዮጵያ መንግስት ግንኙነቱን እያጠናከረ መገኘቱም የውጭ ምንዛሪ ያስገኛል የሚል እምነት ተጥሎበታል።
ይህ ደግሞ ሌላ ያልተጠበቁ ሁኔታዎችን እያስከተለ መሆኑ ታውቋል።
በዚህም ኳታር ላይ በዋናነት ከተነሱት ሀገራት አንዷ የሆነችው ዩናይትድ አረብ ኢምሬት ከዚህ ቀደም ለኢትዮጵያ በዱቤ ነዳጅ የሰጠችበትን 400 ሚሊየን ዶላር እንዲከፈላት ጠይቃለች።