በአውስትራልያ ብሪዝቤን ከተማ የወልቃይትን ህዝብ የማንነት ጥያቄን ተከትሎ ገዢው መንግስት በህዝቡ ላይ የወሰደውንና እየወሰደ ያለውን እርምጃ የተመለከተ ውይይት ተካሄደ።

ሐምሌ  ፲፱ ( አሥራ ዘጠኝ ) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- ቅዳሜ ሃምሌ 16 2008 ዓ ም በ ኢትዮጵያውያን በተጠራው በዚህ ስብሰባ ላይ በተለይ የወልቃይት አካባቢ ተወላጆችና የጉዳዩ ባለቤቶች የሆኑ ነዋሪዎች የችግሩን አነሳስና ሂደት ምን እንደሚመስል በጥልቀትና በስፋት ለተሰብሳቢው ያስረዱ ሲሆን ከታሪክ እያጣቀሱና የአይን እማኝነታቸውን እያከሉ ስፋ ያለ ገለጻ አድርገዋል።

የአካባቢው ተወላጅ የሆኑትና ስብሰባውን ከጠሩት ኢትዮጵያውያኑ መሃከል አንዱ የሆኑት አቶ ፈረደ መብራቱ ፣  ህወሃት የወልቃይት ተወላጆችን መግደልና ማፈናቀል የጀመረው በ1971ና 72 ዓም አካባቢ መሆኑን  ፣  በወቅቱ ህዝቡ እራሱን እየተከላከለ ሲብስበትም ሲሰደድ መቆየቱን አውስተዋል። በዚህ ሁኔታም በ100ዎች የሚቆጠሩ የአካባቢው ተወላጆች ህይወታቸውን ማጣታቸውንና በሺዎች የሚቆጠሩት ቀያቸውን ጥለው እንዲሰደዱ መገደዳቸውን በማስረጃ የተደገፈ ማብራሪያ አቅርበዋል።

ወላጅ አባታቸውንና ወንድማቸውን በተመሳሳይ ሁኔታ እንዳጡ የገለጹት አቶ ፈረደ፣ ሌሎችም የአካባቢው ተወላጅም ሁኔታ ከሳቸው ያልተለየ እንደሆነ አስረድተዋል። ስርዓቱ ስልጣን ከያዘበት ግዜ ጀምሮ በጋምቤላ ኦሮሞና በአጠቃላይ ኢትዮጵያውያን ላይ መጠነ ሰፊ ግድያና አፈና መፈጸሙን ያወሱ ሲሆን፣  የወልቃይትን ለየት የሚያደርገው ግድያውና አፈናው ህወሃት ስልጣን ሳይዝ ገና በበረሃ እያለ መጀመሩ ነው ብለዋል። አቶ ፈረደ እንዳስረዱት የአካባቢው ማህበረሰብ አያት ቅድመ አያቶቹ ያቆዩለትን መሬት ጠብቆ ለማቆየት ከህይወት መሰዋእትነት አንስቶ የተቻለውን ሁሉ ማድረጉንና በማድረግ ላይ እንደሚገኝ አክለዋል።

ህወሃት ስልጣን ላይ ከወጣ በኋላ የአካባቢው ተወላጆች በመረጣቸው ኮሚቴዎቹ አማካኝነት የፌዴረሽን ምክር ቤትን ጨምሮ ጉዳዩ ይመለከተዋል የተባሉ መንግስታዊ ተቋማት ጋር ሁሉ አቤት ማለታቸውን አውስተው ይሁን እንጂ ለጥያቄያቸው መልስ ከመስጠት ይልቅ የህወሃት ሰዎች በዳንሻ በሁመራና በሌሎ ችም ቦታዎች የኮሚቴ አባላቱን እየተከታተሉ  ማዋከብና ማሰቃየት ብሎም እያፈኑ መውሰድ መጀመራቸው አሁን ለተነሳው የህዝብ እንቅስቃሴ ምክንታይ መሆኑን አቶ ፈረደ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ  ማህበር በኪዊንስላንድ ፕሬዝዳንትና ከዝግጅት አስተባባሪዎች አንዱ የሆኑት አቶ አንተነህ ሽፈራው ፣ የህወሃት መንግስት ወደስልጣን ከመጣበት ግዜ አንስቶ የአማራ ህዝብ በምንም መልኩ እውነተኛ ተወካይ እንዳይኖረው ሲታፈን መቆየቱን ወደኋላ በማስታወስ ለተሰብሳቢው አብራርተዋል።

የእለቱ የመድረክ መሪና ከዝግጅቱ አስተባባሪዎች አንዱ የሆኑት አቶ መኩሪያው ሽፈራው በበኩላቸው፣  በጎንደር ስለተገደሉት ንጹሃንን ጭምሮ በኦሮሞ ወገኖቻችን ላይ የተፈጸመውን ግድያና መጠነ ሰፊ እስራት፤ በጋምቤላ ከወላጆቻቸው ስር ተነጥቀው ስለተወሰዱት ህጻናት እንዲሁም በቅርቡ በአዲስ አበባ በተለይም ላፍቶ አካባቢ በዚህ ክረምት ቤታቸው በላያቸው እንዲፈስርባቸው ተደርገው አራስ ፣ ህጻናት ልጆች ጭምር ለጎዳና ህይወት የተዳረጉበትን ክስተት በማውሳት ይህ ሁሉ ግፍና መከራ በወገኖቻችን ላይ ሲደርስ በጋራ ቆመን ከመታገል ይልቅ በትንንሽ ምክንያቶች እየተለያየን የወገናችንን መከራ አራዝመነዋል በማለት  በቁጭት ተናግረዋል።  የግል ምቾት የወገንን በደል እንዳናስብ ሊያደርገን አይገባም ያለው አቶ መኩሪያው፣  ኢትዮጵያዊነት በጋራ መቆም ነው ሲሉ አክለዋል።

ከተሰብሳቢዎቹም በርካታ ሃሳቦች ተነስተው ውይይት የተካሄደባቸው ሲሆን ለተነሱ ጥያቄዎችም ከመድረክ ምላሽ ተሰጥቶባቸዋል። በእለቱ የሴቶች ተሳትፎ ጠንካራ እንደነበር ኤልሳቤጥ ግዛው ከአውስትራሊያ ዘግባለች።