ኢሳት (መስከረም 23: 2009)
ነዋሪነታቸው በአውስትራሊያ የሆነ ኢትዮጵያውያን የሃገሪቱ መንግስት በኢትዮጵያ በመፈጸም ላይ ነው ያሉትን የሩዋንዳ አይነት የዘር ማጥፋፍ ድርጊት ለማስቆም ዕርምጃ እንዲወስድ መጠየቃቸውን የአውስትራሊያ መገናኛ ብዙሃን ሰኞ ዘገቡ።
ዕሁድ በቢሾፍቱ ከተማ ለበርካታ ሰዎች ሞት ምክንያት የሆነውን ተቃውሞ ተከትሎ በመዲናይቱ ሲድኒ ከተማ የሃዘን መግለጫ ስነስርዓትን ያካሄዱት ኢትዮጵያውያን በስልጣን ላይ ያለው ገዢው የኢህአዴግ መንግስት በዘር ማጥፋት ድርጊት መሰማራቱን እንደገለጸ SBS የቴሌቪዥን ጣቢያ ዘግቧል።
ኢትዮጵያውያኑ በኢትዮጵያ መንግስት ይፈጸማል ያሉትን የሩዋንዳ አይነት የዘር ማጥፋት ድርጊት የአውስትራሊያ መንግስት ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እርምጃን እንዲወስድና ከጎናቸው እንዲቆም አሳስበዋል።
አቶ ተስፋዬ እንግዳ ወርቅ የተባሉ የከተማዋ ነዋሪ በኢትዮጵያ መንግስት የጅምላ ግድያ በመፈጸም ላይ በመሆኑ የምዕራባውያን ሃገራት ጣልቃ መግባት እንደሚኖርባቸው ለቴለቪዥን ጣቢያው አስረድቷል።
የአውስትራሊያ መንግስት በኢትዮጵያ ያለውን የሰብዓዊ መብት ጥሰትና ግዳያ በመገምገም ከሃገሪቱ ጋር ያለውን ግንኙነት መመርመር እንደሚገባው ኢትዮጵያውያኑ ጥያቄ ማቅረባቸው ታውቋል።
የአውስትራሊያ መንግስት ለኢትዮጵያ የሚሰጠው ድጋፍ ለፖለቲካ አላማ መዋል እንደሌለበት የማረጋገጥ ሃላፊነት አለበት ሲሉ አቶ ሰለሞን ከበደ የተባሉ የሲድኒ ነዋሪ ለዜና ማሰራጫው ገልጿል።
ኢትዮጵያውያኑ ላቀረቡት ጥያቄ ምላሹን የሰጠው የአውስትራሊያ መንግስት በበኩሉ በሃገሪቱ ላይ እየቀረቡ ያሉ የሰብዓዊ መብት ጥያቄዎችን በመከታተል ላይ መሆኑን አስታውቋል።
የሃገሪቱ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርት ቃል አቀባይ አውስትራሊያ ያላትን የሰብዓዊ መብት ስጋት አጀንዳ በማድረግ በተደጋጋሚ ከኢትዮጵያ ባለስልጣናት ጋር መወያየቱን ለዜና አውታሩ በሰጡት ምላሽ አመልክቷል።
ዕሁድ ቢሾፍቱ ከተማ ለበርካታ ሰዎች ሞት ምክንያት የሆነውን ይህንኑ ተቃውሞ ተከትሎ በተለያዩ የአለማችን ሃገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ያላቸውን ሃዘን እየገለጹ ይገኛል።