ኢሳት ዜና (ነሐሴ 15 ፣ 2007)
ሰሞኑን በኢትዮጵያ አየር መንገድ የመንገደኞ አውሮፕላን ውስጥ በእቃ መጫኛ ውስጥ ተደብቆ በስዊድን ጥገኝነትን የጠየቀው ኢትዮጵያ በአየር መንገድ ውስጥ በአንድ ብሄር የበላይነት የሚደርሰው በደልና ግፍ ለህዝብ ለማጋለጥ ሲል ድርጊቱን መፈጸሙን ከኢሳት ጋር ባደረገው ቃለ ምልልስ አስታወቀ።
የ 24 አመቱ ወጣት ይርጋሸዋ ማሽላ በኢትዮጵያ አየር መንገድ ውስጥ ለመናገር የሚከብድ የአንድ ብሄር የበላይነት ሰፍኖ እንደሚገኝ እና በአየር መንገዱ ውስጥ ለመናገር የሚከብድ የአንድ ብሄር የበላይነት ሰፍኖ በሚገኝ እስር ቤት ለሁለት ቀን መታሰሩን ገልጿል።
በኢትዮጵያ አየር መንገድ የእቃ ማጓጓዣ ክፍል ውስጥ ሰራተኞች የነበረው ወጣት ይርጋሸዋ በስራው ላይ ያለ እስክሪን ፍተሻ ያለፈ የአንዲት ኢትዮጵያዊ ሻንጣ ተከፍቶ መገመት የሚቸግረው ዶላር መታየቱንና የጸጥታ ሀይሎች ሻንጣውን አውቀህ ነው የከፈትከው በሚል ለእስር እንደዳረጉት አስረድቷል።
ከኢትዮጵያ ሊወጣ የነበረውን ሻንጣ መከፈት ተከትሎም ወጣቱ በአየር መንገድ ውስጥ በሚገኝ ልዩ እስር ቤት ለሁለት ቀን ያለ-ምግብ እና ውሃ ታስሮ መቆየቱን በቃለ ምልልሱ ገልጿል።
አቶ ጦናይ የተባሉ የአየር መንገዱ የጸጥታ ክፍል ሀላፊ ወጣቱ ያየውን ሁኔታ ለሌላ ሰው ከተናገረ በቤተሰቡ ላይ ስደጋ እንደሚደርስበት አሳስበውት እንደነበር አመልክቷል። ለ 8 ሰአታት ያህል በአውሮፕላኑ የእቃ መጫኛ ክፍል ውስጥ ተደብቆ በስዊድን የፖለቲካ ጥገኝነትን ያቀረበው የአየር መንገዱ ሰራተኛ ትምህርታቸውን በአግባቡ ያላጠናቀቁ የአንድ ብሄር ተወላጆች በአየር መንገዱ ዋና ዋና ቦታዎች ተመድበው እንደሚገኙም ገልጸዋል።
በአየር መንገዱ ለሁለት አመታት ያየውን ግፍና በደል እንዲሁም የአንድ ብሄር የበላይነት በመቃወምና ጉዳዩን ለህዝብ ለማጋለጥ ሲል ህይወቱን አደጋ ላይ በሚጥል ሁኔታ ስደት መምረጡን በቃለ ምልልሱ አስረድቷል;
የባለስልጣናት ቤተሰቦችና የቅርብ ጓደኞችም ከሀገር ይዘው የሚወጡትና ወደ ሀገር ይዘው የሚገቡት ሻንጣ ምንም ፍተሻ እንደማይደረግበት የፖለቲካ ጥገኝነቱን አቅርቦ የሚገኘው ወጣት ይርጋሸዋ አክሎ ገልጿል።
በጉዞው ወቅት በእቃዎች መጫን ምክንያት መጠነኛ ጉዳት ደርሶበት እንደነበር የተናገረው የአየር መንገዱ የቀድሞ ሰራተኛ ህይወቱ በተአምር ተርፎ በኢትዮጵያ ውስጥ በገዢው የኢህአዴግ መንግስት የሚፈጸመውን በደል ለሀዝብ ይፋ ለማድረግ በመብቃቱ ደስታ እንደተሰማው ከኢሳት ጋር ባደረገው ቃለ-ምልልስ ገልጿል።