በአውሮፓ ሃገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን በተለያዩ አገራት የሚገኙት የኢትዮጵያ ኤምባሲዎችን ለሰዓታት ተቆጣጠሩ

 

ኢሳት (ጳጉሜ 3 ፥ 2008)

በአውሮፓ ብሪታኒያ፣ ጀርመንና ስዊድን ሃገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያን መንግስት በሰላማዊ ሰዎች ላይ ይፈጽመዋል ያሉትን ግድያና አፈና በመቃወም ሃሙስ በየሃገራቱ የሚገኙ የኢትዮጵያ ኤምባሲዎችን ለሰዓታት ያህል ተቆጣጠሩ።

በሶስቱ ሃገራት በሚገኙ የኢትዮጵያ ኤምባሲዎች ላይ በተመሳሳይ ዕለት እርምጃውን የወሰዱት ኢትዮጵያውያን የተለያዩ ጸረ-መንግስት አድማዎችን ሲያስተጋቡ ማርፈዳቸውን ከየሃገራቱ ለኢሳት የደረሱ መረጃዎች አመልክተዋል።

ስዊድን መዲና ስቶኮልም ከተማ የሚገኘውን የኢትዮጵያ ኤምባሲ ተቆጣጥረው ያረፈዱት ኢትዮጵያውያን “ግድያ ይቁም” “መንግስት ለተፈጸሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ተጠያቂ ነው” የሚሉ ድምጾችን ሲያሰሙ ታይተዋል።

በየኤምባሲዎቹ የተቃውሞ ወረራን ያደረጉት ኢትዮጵያውያን በኤምባሲው ጽ/ቤት ውስጥ የሚገኙ ባለኮከብ ባንዲራዎችን  በማውረድ በአረንጓዴ፣ ቢጫና ቀይ የሰንደቅ አላማ ሲቀይሩ ማርፈዳቸውን እማኞች ለኢሳት ገልጸዋል።

በስቶኮልም ከተማ በሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ተቃውሞን ሲያሰሙ የነበሩት ኢትዮጵያውያን ማስተላለፍ የሚፈልጉትን መልዕክት በአግባቡ ካስተላለፉ በኋላ የኢምባሲውን ህንጻ በሰላም ለቀው መሄዳቸውን አስታውቀዋል።

በወቅቱ በኢምባሲው የነበሩ ዲፕሎማቶችና ሌሎች ሰራተኞች ኢትዮጵያውያኑ ሲያቀርቡ የነበረውን ተቃውሞ በተለያዩ ክፍሎች ውስጥ ሆነው ሲመለከቱ ተስተውለዋል።

በተመሳሳይ ሁኔታም ነዋሪነታቸው በብሪታኒያ ለንደን ከተማ የሆነ ኢትዮጵያውያን ሃሙስ በሀገሪቱ የሚገኘውን የኢትዮጵያ ኤምባሲ ለተወሰነ ሰዓት በመቆጣጠር ተቃውሞን ሲያሰሙ አርፍደዋል።

በኢምባሲው ጽ/ቤት የተገኙት ኢትዮጵያውያኑ የሟች ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊን ፎቶ ግራፍ እንዲሁም ባለኮካቡን ባንዲራ ሲያወርዱ እንዲሁም ጸረ-መንግስት መፈክሮችን ሲያሰሙ አርፈደዋል።

በጀርመን ፍራንክፈርት ከተማ በሚገኘው የኢትዮጵያ ቆንስላ ኢትዮጵያውያን ተመሳሳይ ድርጊት መፈጸማቸው ታውቋል።

ከአንድ አመት በፊት ነዋሪነታቸው በዚህ በአሜሪካ ዋሽንግተን ዲሲ ከተማ የሆነ ኢትዮጵያውያን በኢትዮጵያ ኤምባሲ ውስጥ ተመሳሳይ ድርጊትን መፈጸማቸውን ይታወሳል። በወቅቱ አንድ የኢምባሲው ባልደርባ ጥይትን ተኩሶ የነበረ ሲሆን፣ የአሜሪካ መንግስት ገለሰቡን በ24 ሰዓታት ውስት ሃገሪቱን ለቆ እንዲወጣ ማድረጉ የሚታወቅ ነው።