በአዋሽ ወንዝ ሙላት ከሶስት ሺ ነዋሪዎች በላይ ተፈናቀሉ

ኢሳት (ግንቦት 5 ፥ 2008)

በኢትዮጵያ በተለያዩ ክልሎች እየጣለ ያለው ከባድ ዝናብ ለአዋሽ ወንዝ መሙላት ምክንያት ሆኖ 300ሺ ነዋሪዎች ከቀያቸው ተፈናቀሉ።

በክልሉ አሚባራ ወረዳ የደረሰው ይኸው የጎርፍ አደጋ በተለያዩ መሰረተ ልማቶች ላይም ከባድ ጉዳት ማድረሱን ከሃገር ቤት የተገኘው መረጃ አመልክቷል።

የመከላከያ ሰራዊት አባላትና ሌሎች የነፍስ አድን ሰራተኞችም ነዋርዎችን ለከፋ አደጋ ለመታደግ ርብርብን እያደረጉ የሚገኝ ሲሆን የወንዙ ሙላት በቀጣዮቹ ቀናቶችም እየጨመረ እንደሚሄድ ተሰግቷል።

የተባበሩት መንግስታትና ሌሎች የእርዳታ ድርጅቶች በጎርፍ አደጋ እየተፈናቀሉ ያሉ ሰዎችን በሃገሪቱ ተከስቶ ባለው የድርቅ አደጋ ላይ ተጨማሪ ተፅዕኖን እየፈጠረ እንደሚገኝ መግለጻቸው ይታወሳል።

በቅርቡ በተለያዩ አካባቢዎች በደረሰ የጎርፍ አደጋ በትንሹ 100 ሰዎች መሞታቸው የተገለጸ ሲሆን፣ በቀጣዩ ወራቶችም በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ከቀያቸው ይፈናቀላሉ የሚል ስጋት አይሏል።

ከ100 ሚሊዮን ለሚበልጡ ሰዎች የሚፈለገው የአስቸኳይ የምግብ እርዳታ በበቂ ሁኔታ ባልተገነቡበት ወቅት ተጨማሪ ሰዎች ለእርዳታ በመጋለጥ ላይ መሆናቸው የሰብዓዊ እርዳታ ስራውን ውስብስብ አድርጎት እንደሚገኝም ለመረዳት ተችሏል።

ለተረጂዎች የሚፈለገው አለም አቀፍ ድጋፍ ባለመገኘቱ ምክንያት ወደ ረሃብ ለመሸጋገር አንድ ደረጃ ብቻ ይቀራቸዋል የተባሉ ወረዳዎች ቁጥር 219 መድረሱንም የተባበሩት መንግስታት መረጃ ያመለክታል።

የጎርፍ አደጋ ቀጣይ ከሆነም በሰብል የእርሻ ስራ ላይ ያልተጠበቀ ጉዳት ሊደርስ እንደሚችልና የተረጂዎች ቁጥር ወደ 15 ሚሊዮን ይደርሳል ተብሎም ተሰግቷል።