በአዋሳ ክብር ለእናቶች በሚል በተዘጋጀው በአል ላይ ተሸላሚ እናቶች ሳይገኙ ቀሩ

ሰኔ ፳፮ ( ሃያ ስድስት ) ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- ወኪላችን እንደገለጸው ክብር ለናቶች የልማት ተራድኦ ድርጅት በሀዋሳ መስቀል አደባባይ ፕሮግራም አዘጋጅቶ የነበረ ቢሆንም፣ እውቅናና ሽልማት ይሰጣቸዋል የተባሉ እናቶች ሳይገኙ ፣ በእናቶች ስም የተሰበሰበው ገንዘብ ተበልቷል። በፕሮግራሙ ላይ 50 በሀዋሳ ከተማ የሚኖሩ ልጆቻቸውን ለማሳደግ ዋጋ የከፈሉ እና ዝቅተኛ ኑሮ ላይ የሚገኙ እናቶችን ለመሸለም እና እውቅና ለመስጠት ፕሮግራም ተይዞ የነበረ ቢሆንም፣ ዝግጅቱ እሁድ ምሽት በተጠናቀቀበት ሰአት ይሸለማሉ የተባሉት እናቶች ሳይቀርቡ ቀርተዋል።
እነዚህ ይሸለማሉ የተባሉት እናቶች ከየክፍለከተማው ሴቶችና ህፃናት ቢሮ የመለመላቸው ሲሆኑ፣ በስፓንሰር ደረጃ ደግሞ የክልሉ ማረሚያ ቤቶች ፣ የክልሉ ፀረ ሙስና ቢሮ፣ በርካታ የመንግስት መስሪያ ቤቶችና በአጠቃላይ 32 ድርጅቶች ስፓንሰር አድርገውታል።
አንደኛ ደረጃ ስፓንሰር 60 ሺህ ብር ሲሆን፣ የመጨረሻው ደግሞ 20 ሺህ ብር ነበር ። ይሸለማሉ ተብሎ ሲነገርላቸው የነበሩት እናቶች በዝግጅቱ ላይም እንዲገኙ ግብዣ አልቀረበላቸውም፣ በዝግጅቱ ላይ የተገኘው የሰው ብዛትም ከ 100 አይበልጥም።
በእናቶች ስም የተሰበሰበው ገንዘብ በዚህ ሁኔታ በመበላቱ ብዙዎች ብስጭታቸውን እየገለጹ ነው።