በአወዳይ ከፍተኛ የሰብአዊ ቀውስ አጋጥሟል ተባለ

ሐምሌ  ፳፯ ( ሃያ ሰባት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በኦሮምያ ክልል ምስራቅ ሃረርጌ ዞን አወዳይ ከተማ ባለፈው እሁድ ተነስቶ የነበረውን ተቃውሞ ተከትሎ ከ11 ሰዎች በላይ ከተገደሉ በሁዋላ፣ አካባቢውን የተቆጣጠሩት የመከላከያ ሰራዊት አባላትና የፌደራል ፖሊሶች ማንኛውም ሰው ከቤቱ እንዳይወጣ እገዳ በመጣላቸው፣ ህጻናትና እናቶችን ጨምሮ ህዝቡ ከፍተኛ ስቃይ ውስጥ መግባቱ ታውቋል። ወኪላችን እንደገለጸው አብዛኛው ህዝብ ከቤት አትወጣም በመባሉ የሚበላው አጥቶ ተቸግሯል። እገታው በአስቸኳይ ካልተነሳ ከፍተኛ የሆነ ህዝብ በርሃብና በውሃ ጥም ያልቃል ብሎአል።

ወታደሮቹ ወጣቶችን እያፈሱ ሀረር ቀበሌ 08 ከቴምስ ሆቴል ከፍ ብሎ በሚገኘው የምስራቅ ሃረርጌ ፖሊስ ኮሚሽን ግቢ ውስጥ እያጎሩዋቸው ሲሆን፣ ከመያዝ ያመለጡት ደግሞ በተለያዩ አካባቢዎች ተሸሽገው ይገኛሉ። እስካሁን ድረስ ባለው መረጃ በመቶዎች የሚቆጠሩ ወጣቶች ታስረዋል። መንገዶች አሁንም ተዘጋግተዋል፣ የንግድ ድርጅቶች፣ የመንግስት መስሪያ ቤቶች ተዘግተዋል።መብራት ከጠፋም ሶስተኛ ቀን ተቆጥሯል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ የፌታችን ቅዳሜ በመላው ኦሮምያ የተቃውሞ ሰልፍ ይደረጋል ተብሎ ይጠበቃል። በኦሮምያ የሚካሄደውን ህዝባዊ ተቃውሞ ተከትሎ ከ600 በላይ ዜጎች በአጋዚ ወታደሮች ተገድለዋል። በ10 ሺዎች የሚቆጠሩት ደግሞ ታስረዋል። የኦህዴድ ከፍተኛ አመራሮች በጸጥታ ሃይሎች የሚወሰደውን እርምጃ ከማውገዝ ይልቅ ለጸጥታ ሃይሎች ያላቸውን ደጋፍ በመገናኝ ብዙሃን እየገለጸ ነው።