በአወዳይ በተነሳው ተቃውሞ  ህጻናትን ጨምሮ  በትንሹ 4  ሰዎች ተገደሉ

ሰኔ ፳፬ ( ሃያ አራት ) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በምስራቅ ሃረርጌ በአወዳይ ከተማ የተነሳውን ህዝባዊ ተቃውሞ ተከትሎ የወረዳው አስተዳዳሪ በከፈተው ተኩስ  ሁለት ህጻናት እና  አንድ ጎልማሳ ተገድለዋል። ነዋሪዎች ማምሻውን ለኢሳት እንደገለጹት ከሆነ የሟቾች ቁጥር 7 ድርሷል።

ኢብራሂም ሙሜ የሚባል ባለ ጸጉር ቤት እና አህመድ አልዬ የሚባል ባለሞባይል ቤት አሊ መሰራ ህንጻ እና አዋሽ ባንክ መሃል የሚገኘው ቤታቸው  ምክንያቱ ባልታወቀ ሁኔታ ሌሊት ላይ መቃጠሉን ተከትሎ ህዝቡ ለተጎጂ ቤተሰቦች የእርዳታ ገንዘብ ማሰባሰብ ሲጀምሩ ፖሊሶች ጣልቃ ገብተው ለምን ተሰባሰባችሁ በማለት ተኩስ ከፍተዋል።

የአወዳይ 01 ቀበሌ ሊቀመንበር የሆነው አቶ አብዲ እድሪስ በከፈተው ተኩስ ሁለት ህናጻንት ጨምሮ 3 ሰዎች ተገድልዋል።  ፌደራል ፖሊሶች ደግሞ 4 ሰዎችን መግደላቸውን ነዋሪዎች ተናግረዋል። ትክክለኛውን የሟቾቾችን ቁጥር ለማወቅ ኢሳት ያደረገው ጥረት አልተሰካም።  በድርጊቱ የተበሳጨው ህዝብ ወደ ሊቀመንበሩ ቤት በማምራት ሁለቱንም መኖሪያ ቤቶቹን ያቃጠለ ሲሆን፣ ሊቀመንበሩ ወደ ሃረር ሸሽቶ ሲያመልጥ ፌደራል ፖሊሶች ደግሞ ባለቤቱንና ልጆቹን ይዘው ከከተማ አስወጥተዋቸዋል።

ከጅጅጋ እና ሃረር የተነሱ ተሽከርካሪዎች መንገድ ተዘግቶባቸው  ወደ ሃረር የተመለሱ ሲሆን፣ የመንግስት መስሪያ ቤቶችና ባንኮች ተዘግተው ውለዋል። የተሰባበሩ ተሸከርካሪዎች መኖራቸውንም የአይን እማኞች ገልጸዋል። ሃሮማያ ዩኒቨርስቲ የሚያስተምሩ መምህራን መንገድ በመዘጋቱ ምክንያት ወደ ስራ ሳይሄዱ ወደ ሃረር ተመልሰዋል።

የኦሮሞ ወጣቶች ህዝባዊ እንቅስቃሴ ከተጀመረበት ወቅት ጀምሮ በአካባቢው የሚታየው ተቃውሞ እስካሁን አልቆመም። ተቃውሞችን ተከትሎ በብዙ መቶዎች የሚቆጠሩ ዜጎች በግፍ ተገድለዋል። ሂማንራይትስ ወችና ሌሎችም የሰብአዊ መብት ድርጅቶች ግድያው በገለልለተኛ ወገን እንዲጣራ በመጠየቅ ላይ ናቸው