በአወልያ የተጀመረው ተቃውሞ ዛሬም ቀጥሎ ውሏል

መጋቢት 7 ቀን 2004 ዓ/ ም

ኢሳት ዜና:-ከፍተኛ በሆነ የጸጥታ ቁጥጥር በተካሄደው ተቃውሞ ሙስሊም ኢትዮጵያውያን ጥያቄያቸው መልስ እስከሚያገኝ ድረስ ተቃውሞዋቸውን እንደሚቀጥሉ ገልጠዋል።

አንዳንድ የተመረጡ የኮሚቴው አባላት መንግስት ወደ አወልያ እንዳይሄዱ ከፍተኛ ማስጠንቀቂያ ስለሰጣቸው በግቢው አለመታየታቸው ታውቋል። ይሁን እንጅ የኮሚቴው አባላት ያልሆኑት ሌሎች ሙስሊሞች ንግግር ማድረጋቸው ታውቋል።

የመንግስት የጸጥታ ሀይሎች የሙስሊሙን መሪዎች በደህንነት መኪኖች ሲከታተሉዋቸው መሰንበቱን  ተከትሎ የጸጥታ መደፍረስ ሊከሰት ይችላል ተብሎ የተፈረ ቢሆንም፣ የመንግስት የጸጥታ ሀይሎች ሙስሊሙ በአወልያ እንዳይገኝ ለማገድ ባለመሞከራቸው የተፈራው ረብሻ አልተፈጠረም።

የፌደራል ጉዳዮች ሚኒሰትር የሆኑት አቶ ሽፈራው ተክለማርያም ከእንግዲህ በአወልያ ምንም አይነት  ተቃውሞ እንዳይካሄድ ማዘዛቸው ይታወሳል። ይሁን እንጅ በዛሬው እለት የታየው ተቃውሞ የሚኒሰትሩን ትእዛዝ ዋጋ ቢስ የሚያደርግ ነው።

በሌላ ዜና ደግሞ አልቃይዳ  በሚያስደነግጥ ሁኔታ በየመን ድል በመቀዳጀት ላይ እንዳለና በደቡብ የሚገኙ ከተማዎችን መቆጣጠሩን የተባበሩት መንግሰታት ድርጅት መልእክተኛ መግለፃቸዉን ዩናይትድ ፕሬስ ኢንተርናሽናል (UPI)  የዜና ወኪል አስታዉቋል። መልእክተኛዉ ሊባኖስ ቤይሩት ዉስጥ በሰጡት ማስጠንቀቂያ የአሜሪካን የአየር ድብደባ መሪዎቹን በመልቀም ላይ ቢሆንም የአማፂዉ ቡድን ኢራቅና ሰሜን አፍሪቃ ዉስጥ ጥቃት ለመፈፀም በማንሰራራት ላይ እንደሚገኝ ተናግረዋል። 

የሱኒ ሙስሊም ድርጅት ላለፉት አስርት አመታት የነበረዉን አለመግባባት በማስወገድ ከኢራኑ ሺአይት ጋር የይስሙላ ህብረት ሊመሰርት ይችላል የሚል ወሬ በሚናፈስበት በዚህ ወቅት ሱኒ ሙስሊም በሶሪያ፤ በሊባኖስ፤ በግብፅና በኢትዮጵያ ሳይቀር ጭንቅላቱን በማቅናት ላይ እንዳለ የመንግስታቱ ድርጅት ልዩ መልእክተኛ ጀማል ቤኖማርን ገልፀዋል።

በየመን ለ33 አመታት በስልጣን ላይ የነበሩት ፕሬዝዳንት አሊ አብዱላህ ሳላህ በአፍቃሬ ዲሞክራሲ ሃይሎች እንቅስቃሴ ከተወገዱ በሁዋላ በደቡብ የመን እየገፋ የመጣዉ የአልቃይዳ እንቅስቃሴ ለተባበሩት መንግስታት ድርጅት የፀጥታዉ ምክር ቤት በሚስጥር የተገለፀዉ ባለፈዉ አርብ ነዉ።

የሪፖርቱ ግልባጭ የደረሰዉ የዋሺንግተን ፖስት ጋዜጣ  አልቃይዳ በአረብ የባህር ወሽመጥ የመን ዉስጥ በቅርቡ በማድረስ ላይ ያለዉ የጥቃት መጠን አማፂዉ እስላማዊ ቡድን አስፈሪ የፀጥታ ስጋት ሊሆን እንሚችል የሚያሳይ መሆኑን መልእክተኛዉን ጀማል ቤኖማርን በመጥቀስ አስታዉቋል።  

___________________________________________________________________________________________________________________________________________________________________________

ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.

ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide