መጋቢት 4 ቀን 2004 ዓ/ ም
ኢሳት ዜና:-የአወሊያ መስኪድን እንቅስቃሴ የሚመሩት የሀይማኖት መሪዎች በደህንነት ሀይሎች እየተዋከቡ ነው
የኢሳት የመረጃ ምንጮች እንደገለጡት በአወልያ የተጀመረውን የሙስሊም ኢትዮጵያውያንን እንቅስቃሴ በበላይነት የሚያስተባብሩት መሪዎች ካለፈው አርብ ጀምሮ በደህንነት ሀይሎች እየተዋከቡ ነው። ትናንት 7 የደህንነት መኪኖች የተቃውሞው ዋና መሪ የሚባሉትን የኡስታዝ አቡበክርን መኪና ሲከተሉ ውለዋል። በእየአንዳንዱ መኪና ውስጥም ከ2 እስከ 3 የሚደርሱ የደህንነት አባላት ነበሩ። ዛሬ ሊሊቱን የኡስታዝ አቡበክር ቤት በደህንነት ሀይሎች ተከቦ አድሯል። የኢሳት የመረጃ ምንጮች የተለያዩ የእምነቱ መሪዎችን ሲከታተሉ የዋሉትን የደህንነት መኪናዎችን የመለያ ዝርዝር የላኩ ሲሆን ፣ ኡስታዝ አቡበክርን ሲከታተሉ ከዋሉት መኪኖች መካከል ቶዮታ ኮሮላ አዲስ አበባ የጎን ቁጥር 2፣ ታርጋ ቁጥር 40674፣ 71580፣ 47376፣76847፣ ቶዮታ ቴራስ የጎን ቁጥር 2 ታርጋ ቁጥር 70478 እንዲሁም ኒሳን ሰኒ የጎን ቁጥር 3 አዲስ አበባ ይገኙበታል።
የመንግስት እርምጃ ሙስሊሙ በመጪው አርብ በአወሊያ ተገኝቶ ተመሳሳይ ተቃውሞ እንዳያሰማ ከወዲሁ ለመከላከል ነው ተብሎአል። አንድ ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ ሰው ለዘጋቢያችን እንደገለጡት፣ ማዋከቡና ማስፈራራቱ በ1997 ምርጫ ወቅት በቅንጅት መሪዎች ላይ ይደረግ ከነበረው ጋር ተመሳሳይ ነው፤ መንግስት ለሙስሊሙ ጥያቄ አጥጋቢ መልስ እንደመስጠት በሀይልና በማስፈራራት ለመመለስ የሚያደርገው ሙከራ ሙስሊሙን ይበልጥ የሚያስቆጣና ወደ አልተፈለገ ብጥብጥ የሚወስድ ነው።
እርሳቸው እንዳሉት የእምነቱ መሪዎችን ማዋከቡና ማስፈራራቱ እንደቀጠለ ቢሆንም፣ መሪዎቹ ግን በመንግስት ማስፈራሪያ ተደናግጠው ጥያቄያቸውን በህግ መድረክ እና በሰላማዊ መንገድ ከማራመድ ወደ ሁዋላ አላሉም ብሎአል።
ኢሳት በዚህ ሳምንት መሪዎችንና ቀስቃሽ የተባሉትን ማዋከብ ሊጀመር እንደሚችል ማስጠንቀቁ ይታወሳል።
___________________________________________________________________________________________________________________________________________________________________________
ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.
ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide