(ኢሳት ዜና–ሐምሌ 28/2009) በአንድ ወጣት ልጆቻቸው የተደፈሩባቸው ወላጆች ፍትህ ማግኘት እንዳልቻሉ ገለጹ።
በአዲስ አበባ ጉለሌ አባዲና ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ከ6 እስከ 8 አመት የሚሆናቸውን ዘጠኝ ህጻናት ወንዶችን የደፈረው ወጣት በእስር ላይ ቢሆንም እስካሁን ግን ፍትህ እንዳላገኙ ቤተሰቦቻቸው ተናግረዋል።
የተደፈሩት ህጻናት ለከፍተኛ የጤናና የስነልቦና ችግር ተዳርገዋል።
ሽንትና አይነምድራቸውን መቆጣጠር አልቻሉም።ወላጆቻቸው እንደሚሉት ህጻናቱን የደፈረው ወጣት ወላጅ አባት እያስፈራሯቸው ነው።
በልጆቻቸው ላይ ከደረሰው አደጋ በተጨማሪ የአካባቢው ማህበረሰብ እያገለላቸው እንደሆነም ገልጸዋል።የሕጻናቱ ወላጆች የኢትዮጵያ ህዝብ ድጋፍ እንዲያደርግላቸው ጥሪ አቅርበዋል።
ለሰማው አስደንጋጭ ነው።ከኢትዮጵያዊ ባህልና ስነምግባር አንጻር ጉዳዩ ለብዙዎች አስፈሪ ሊሆን ይችላል።በጉለሌ አካባቢ ልዩ ቦታው አባዲና የተፈጸመው ወንጀል ህጻናቱን ለከፍተኛ አደጋ ቤተሰቦቻቸውን ለእንግልትና ስቃይ ዳርጓል።
ከምንም በላይ ደግሞ ለተፈጸመባቸው በደል ፍትህ የማጣቱ ጉዳይ ለወላጆቻቸው ተጨማሪ በደል ሆኗል።
የሁለተኛ ደረጃ ተማሪ የሆነው ወጣት የአካባቢው ሕጻናትን በተለያዩ ጊዜያት ደፍሯቸዋል።ይህን ደግም ወላጆቻቸው አላወቁም።ህጻናቱም አልተናገሩም።ከስድስት እስከ ዘጠኝ አመት የሚሆናቸውን እነዚህን የአንድ አካባቢ ህጻናት ወንዶችን እይስፈራራ ድርጊቱን እንደሚፈጽም ነው የተረጋገጠው።የአንዱ ልጅ እናት ለኢሳት እንደተናገሩት ልጃቸው የተፈጸመበትን ድርጊት ያወቁት ከቆየ በኋላ ነው።
በጤንነቱ ላይ ችግር ተፈጥሮ ሽንትና አይነ ምድሩን መቆጣጠር ሲያቅተው ችግሩ ሌላ ነገር እንጂ ይህ ይፈጸማል የሚል ነገር አስበውም እያውቁም ነበር።
የአንደኛው ሕጻን ወላጅ እናት እንደሚሉት በልጃቸው ላይ የደረሰው እሳቸው እጅ ከፍንጅ ከያዙ በኋላ ጉዳዩ በአካባቢው ህዝብ ጆሮ ደረሰ።
ሌሎች ተመሳሳይ ጥቃት የተፈጸመባቸው ተገኙና ጉዳዩ መነጋገሪያ ሆነ።በፖሊስ ዘንድም ታወቀ።
የዛሬ አመት አካባቢ ዘጠኙን ሕጻናት በተለያዩ ጊዜያት ደፍሯል የተባለው ወጣት በቁጥጥር ስር ዋለ።
ነገር ግን ፍትህ እስከዛሬ ሊገኝ ባለመቻሉ ወላጆች የፍትህ ያለህ ጥሪያቸውን ማሰማት ጀመሩ።
የከፋው ደግሞ የእነዚህን ሕጻናት ወላጆች ቤታቸው ድረስ በመሄድ ልጄን አሳሰራችሁብኝ እያሉ እያስፈራሩ እስከ ምደብደብና የአካል ጉዳት ያደረሱት የደፋሪው ወላጅ አባት ጉዳይ ነው።
ገንዘብ ስላላቸው ያንን ተመክተው በየቤታቸው እየመጡ ያስፈራሩናል ይደበድቡናል።የሚል ክስ ከተጎጂ ህጻናቱ ወላጆች ይሰማል።እኚሁ የተከሳሽ አባት የአንዱ ሕጻን እናት ላይ ድብደባ በመፈጸማቸው ታስረው እንደሚገኙ ታውቋል።
በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ህጻናቱ መደፈራቸውን በህክምና ማስረጃ ቢረጋገጥም ጉዳዩን ለፍርድ ለማቅረብ ሳይቻል ከአንድ አመት በላይ መቆየቱ አነጋጋሪ ሆኗል።
ህጻናቱ ለከፍተኛ የጤንነት ችግር በመዳረጋቸው አቅመ ደካማ የሆኑት ወላጆቻቸው ማሳከም አልቻሉም።
ችግሩ የስነ ልቦና ጉዳትም በማስከተሉ ወላጆቻቸው ከፍተኛ ጭንቀት ውስጥ መሆናቸው ታውቋል።እናት የልጆቻቸውን ጉዳት ይናገራሉ።
ወጣት ኢዩኤልና ወጣት ረቂቅ ከሌሎች ጋር በመሆን ፍትህ የሚያገኙበትን ህጻናቱም ህክምና አግኝተው የሚፈወሱበትን እርዳታ ፍለጋ በበጎ ፈቃደኝነት እየሰሩ ናቸው።
የልጆቹ ስቃይ ቃላት ከሚገልጸው በላይ ሆኖባቸዋል።ፍትህ ማጣት ግን ሌላው ጉዳት እንደሆነባቸው ነው የሚናገሩት።
ጉዳዩ በመንግስት በኩል ችላ የተባለበት ምክንያት አልታወቀም።የህጻናቱ ወላጆች ስጋት ላይ ናቸው።የኢትዮጵያ ህዝብን ድጋፍ ይሻሉ።