ኢሳት ዜና (ሃምሌ 24, 2007)
በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ከ 40 በላይ የአየር ሀይል ባለሙያዎችና ሰራተኞች በስልጣን ላይ ያለውን ሰርአት በመክዳት ወደተለያዩ ቦታዎች መሰወራቸው ታወቀ ።
የኢሳት የአየር ሀይል ምንጮች እንደገለጹት የደብረዘይት አየር ሀይል ጠቅላይ መምሪያ በወታደራዊ የስራ መደብ የሚያገለግሉትን ጨምሮ 14 ቴክኒሺያኖችና ለጊዜው በቁጥር ያልተገለጹ አብራሪዎች ባለፈው አንድ ወር በስራ ገበታቸው አልተገኙም። በዋና ማዘዢያ ጣቢያና በዘመቻ መምሪያ የአየር ሀይል ባልደረቦች የገቡበት እንዳልታወቀ የደረሰን መረጃ ያመለክታል። 14ቱ ቴክኒሺያኖች በትራንስፖርት እና ስኳድሮን ሄሊኮፕተሮች : በ su 27 በአንቶኖቭ 12 ላይ የሚሰሩ እንደሆኑም ለማወቅ ተችሏል።
በዚህ ወር ውስጥ ከ40 በላይ ሰራተኞችና ባለሙያዎች ስርአቱን ከድተው መሰወራቸውን በመንግስት በኩል በጥብቅና ሚስጥራዊ በሆነ ትእዛዝ እንዲታደኑ እንቅስቃሴ የተጀመረ ሲሆን አብዛኞቹ ካገር የወጡ በመሆናቸው እስካሁን የተያዘ እንደሌለ በደረሰን መረጃ ላይ ተብራርቷል። የከዱት የአየር ሀይል ባለሙያዎች ተቃዋሚዎችን ሳይቀላቀሉ እንደማይቀሩ ምንጮች የገለጹ ሲሆን በአንድ ወር ይህን ያህል ባለሙያ መክዳቱ ለአየር ሀይሉ ኪሳራ እንደሚሆን ይነገራል ።
ከ 1997 ምርጫ ወዲህ ከ 30 በላይ አብራሪዎች ስራቱን ከድተው የተለያዩ ሀገራት የኮበለሉ ሲሆን ባለፈው m35 ሶስት የአየር ሀይል ከፍተኛ ባለሙያዎች መሰወራቸው የታወሳል ።