(ኢሳት ዲሲ–ሕዳር 17/2011) በትግራይ ክልል የ8 ከተሞች ነዋሪዎች ባንድ ብሔር ላይ ብቻ ያነጣጠረ ፖለቲካዊ ጥቃትን እንቃወማለን ሲሉ ሰላማዊ ሰልፍ አደረጉ።
ሰላማዊ ሰልፈኞቹ በፌዴራል መንግስት የትግራይን ህዝብ ለማንበርክ የሚደረግ ሴራ ተቀባይነት የለውም ብለዋል።
በኢትዮጵያ ግድያና የሰብአዊ መብት ጥሰት ሲፈጸም በነበረ ጊዜ በትግራይ ክልል አንድም ጊዜ የተቃውሞ ሰልፍ አለመካሄዱ ይታወሳል።
በትግራይ በሚገኙ 8 ከተሞች የተካሄደው ሰላማዊ ሰልፍ በክልሉ መንግስት በቅርቡ የወጣውን የአቋም መግለጫ የሚደግፍ ነው።
በቅርቡ በትግራይ ክልላዊ መንግስት የወጣው መግለጫ እንደሚያመለክተው በፌዴራል መንግስት ሕግን በማስከበር ስም የትግራይን ሕዝብ ለማንበርከክ ተጽእኖ እየተደረገ ነው።
በሌብነትና ስርቆት ተጠርጥረው የተያዙት ጂኔራል ክንፈ ዳኘው እጃቸው በሰንሰለት ታስረው በሄልኮፕተር ሲወሰዱ በቴሊቪዥን መታየታቸውም ከህግ ይልቅ ፖለቲካዊ ድራማ ነው በማለት የትግራይ ክልል ምክትል ፕሬዝዳንት ዶር ደብረጺዮን ገብረሚካኤል መግለጻቸው ይታወሳል።
የውጭ ጣልቃ ገብነት አለ ማለታቸውም አይዘነጋም።
ይሕንኑ የትግራይ መንግስት አቋም መነሻ በማድረግም በክልሉ 8 ከተሞች የድጋፍ ሰልፍ ተካሂዷል።
ሰላማዊ ሰልፎቹ የተካሄዱትም በሴቲት ሑመራ ፣በአክሱም ፣ በዓድዋና በተምቤን ዓብዪ ዓዲ ከተሞች እንዲሁም በእምባ ኣላጀ ፣ራያ ዓዘቦ ፣ እንዳ መኾኒ ፣ኮረም ፣ኦፍላ ፣በራያ አላማጣ መሆኑ ነው የተገለጸው።
የትግራይን ህዝብ ለማንበርክ የሚደረግ ሴራ ተቀባይነት የለውም፥ በሁሉም የአገሪቱ ኣከባቢዎች ህግ በእኩልነት ይከበር የሚሉና ሌሎቸ እንበረከክም የሚሉ መፈክሮች ሲስተጋቡ ነበር።
ፍትህ ለሁሉ ፣ህገ መንግስት ይከበር የሚሉ መፈክሮችም ተሰምተዋል።ባንድ ብሄር ላይ ብቻ ያነጣጠረ ፖለቲካዊ ጥቃትን እንቃወማለን ያሉት ሰልፈኞቹ ሕግ የሚከበር ከሆነ በሁሉም አካባቢዎች ሊሆን ይገባል ብለዋል።
የሟቹን ጠቅላይ ሚንስትር አቶ መለስ ዜናዊ ፎቶ በመያዝ ሰላማዊ ሰልፍ ካደረጉ የትግራይ ነዋሪዎች መካከል ጠመንጃ ይዘው የወጡ እንደነበሩበትም ለማወቅ ተችሏል።
በሀገሪቱ ህግ ጠምንጃ ይዞ ሰላማዊ ሰልፍ ማድረግ ክልክል ቢሆንም ለነሱ ግን የተፈቀደ ነበር።
በራያና ወልቃይትም ሕዝቡ የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄ እንጂ የማንነት ጥያቄ የለውም ሲሉም ጩሀታቸውን አሰምተዋል።የውጭ ጣልቃ ገብነትንም እናወግዛለን ያሉት።
በኢትዮጵያ ግድያና የሰባዊ መብት ሲፈጸም በነበረ ጊዜ በትግራይ ክልል ውስጥ አንድም የተቃውሞ ሰልፍ አለመካሄዱ ይታወሳል።