ሐምሌ ፲፭ ( አሥራ አምስት ) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በኦሮምያ ክልል በሰሜን ሸዋ ዞን በደራ ወረዳ ወረ መነዬ ቀበሌ ካለፈው ሁለት ሳምንት ጀምሮ በተነሳው የኮሌራ በሽታ 30 ሰዎች ሲሞቱ 94 ሰዎች ደግሞ በበሽታው ተይዘው እየታከሙ ነው። የአካባቢው ባለሙያዎች መረጃውን እንዳያወጡ ማስጠንቀቂያ የተሰጣቸው መሆኑን የገለጹት የኢሳት ምንጮች፣ በሽታው ወደ አጎራባች አካባቢዎች እየተዛመተ መሆኑንም ተናግረዋል።
በርካታ በሽተኞች ወደ ጸበል መሄዳቸውን ተከትሎ በአካባቢው የሚገኘው ጸበል እንዲዘጋም ተደርጓል። በአዲስ አበባ የሚታየው የኮሌራ በሽታ እየቀነሰ የመጣ ቢመስልም በኦሮምያ ግን በሽታው በአስከፊ ሁኔታ እየተስፋፋ ነው።