በአንድ ሆስፒታል በተነሳ የእሳት ቃጠሎ በትንሹ 37 ሰዎች ሞቱ

(ኢሳት ዲሲ–ጥር 18/2010)

በደቡብ ኮሪያ በአንድ ሆስፒታል ውስጥ በተነሳ የእሳት ቃጠሎ በትንሹ የ37 ሰዎች ሕይወት ሲያልፍ በርካታ ሰዎች ቆሰሉ።

ከደረሰው አደጋ ጋር በተያያዘ የሆስፒታሉ ባለቤትና ስራ አስኪያጁ በቁጥጥር ስር ውለዋል።

ከሕሙማኑ በተጨማሪ የሕክምና ባለሙያዎችም በአደጋው ሕይወታቸው አልፏል።

ከደቡብ ኮሪያ ርዕሰ መዲና ሴኡል በ270 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው ሚሪያንግ ከተማ በሚገኘው ሲአንግ ሆስፒታል ትላንት ምሽት የደረሰው የእሳት አደጋ መንስኤ ባይታወቅም በሆስፒታሉ በህክምና ላይ የሚገኙ ህሙማንን ጨምሮ በማቆያ የሚገኙ አዛውንቶችና የሕክምና ባለሙያዎች ሕይወታቸው አልፏል።

የእሳት አደጋ ተከላካይ ሰራተኞች እንደሚገልጹት 200 ያህል ሕሙማን በሚገኙበት ሲአንግ ሆስፒታል 37 ሰዎች ሲሞቱ 70 ያህሉ ቆስለዋል።

የሟቾቹ ቁጥር ሊጨምር ይችላል የሚል ስጋትን በፈጠረው በዚህ አደጋ ብዙዎቹ ሕይወታቸው ያለፈው በጭስ ታፍነው እንደሆነም ተገልጿል።

አንድ የሕክምና ዶክተር እንዲሁም ነርስና የጤና ረዳት ከሟቾቹ ውስጥ እንደሚገኙበትም ታውቋል።

በደቡብ ኮሪያ የቅርብ አመታት ታሪክ ያልተመዘገበ የተባለውን ይህንን አደጋ ተከትሎ የደቡብ ኮሪያው ፕሬዝዳንት ሙን ጄ ኢን ካቢኔያቸውን አስቸኳይ ስብሰባ ጠርተዋል።

የሆስፒታሉ ባለቤትና ስራ አስኪያጅም በቁጥጥር ስር ውለዋል።

ለሆስፒታሉ አስፈላጊው የደህንነት መከላከያ አለመዘጋጀቱ ለእስሩ ምክንያት እንደሆነም ተመልክቷል።

ሆስፒታሉ ከ20 አመት በፊት መገንባቱንም ቢቢሲ በዘገባው አስታውቋል።